ጥቅምት 10 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) አልፎ አልፎ የሚከሰተው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሱ ሰብሎችን እንዳይጎዳ ሁሉን የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ የምርት መሰበሰብ ስራ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የማዕከላዊ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮዎች ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቀዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፤ አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሰ ሰብልን የመጉዳት እና የምርት አሰባሰብ ላይ መስተጓጎል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ እንዲህ አይነቱ ጉዳት እንዳያገጥም የደረሱ ሰብሎች በጊዜ እንዲሰበሰቡ ከቀናት በፊት ክልል አቀፍ ንቅናቄ መደረጉን እና እስከ ቀበሌ ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት የስራ ድርሻ ተከፋፍለው ወደ ተግባር መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የግብርናና የጤና ባለሞያዎች፤ ተማሪዎችና መምህራን፤ እንዲሁም ኮምባይነሮች፣ የመወቅያ ማሽኖችና ሌሎች መሳሪያዎች ያሏቸው የህብረት ስራ ማህበራት እና ባለሀብቶች በምርት ማሰባሰብ ስራው እንዲሳተፉ ክልሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅት ፈጥሮ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የመኸር ምርት በሁሉም አካባቢዎች በተመሳሳይ ጊዜ እንደማይደርስ የተናገሩት ኃላፊው በተለይ በክልሉ ቆላማ እና በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች አብዛኛው ምርት ስለደረሰ፣ ከጥቅምት 15 ጀምሮ የደረሱ ሰብሎችን የመሰብስብ ስራ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ አብዛኛው ሰብል ገና በመድረስ ላይ እንደሆነ የሚገልጹት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ ናቸው፡፡
በዚህ የመኸር ወቅት ከወትሮው በተለየ መልኩ ከፍተኛ የዝናብ መጠን እንደተስተዋለ ገልጸው፤ ምንም እንኳን ከዚህ ወር ጀምሮ ዝናቡ የሚቀንስበት ወቅት ቢሆንም፣ ሳይታሰብ የሚዘንበው ዝናብ የደረሰ ምርትን እንዳይጎዳ ለአርሶ አደሩ የቅድመ ጥንቃቄ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአንዳንድ የክልሉ አከባቢዎች የጤፍ ሰብል መድረሱን ያስታወቁት አቶ አድማሱ፤ የመኸር ምርት አሰባሰብ ስራው ተጀምሮ፣ በዘር ከተሸፈኑ ማሳዎች ምርት ተሰብስቦ እስከሚያቅ ለዝናብና እርጥበት ተጋላጭ የሚሆኑ ሰብሎችን በአስቸኳይ እንዲነሱ፤ ጥንቃቄም እንዲደረግ የማስተማርና ግንዝቤ የማስጨበጥ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ክልሎች ከብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩትና ከክልል ቅርንጫፎች ወቅታዊ የአየር ሁኔታ መረጃ በመከታተል በግብርና ባለሙያዎች አማካኝነት እስከ ቀበሌ ድረስ ምርት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ