የስራ ልምድ በበቂ ሁኔታ እያላቸው የትምህርት ደረጃን አላሟሉም ተብለው ከስራ የሚቀነሱ በርካታ ባለሙያዎች መኖራቸውም ይንገራል ። በዚህም ረጅም አመት ያካበቱትን የስራ ልምድ እንደሃገር የሚታጣበት ሁኔታ መኖሩ ይስተዋላል ።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ባልነበረበት ሁኔታ ፤ ከመደበኛ እውቀት ውጪ ሰዎች ሲሰሩ በማየትና በመልመድ ብቻ የሚገኙ እውቀቶች ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ናቸው የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ ፤
በሃገራችን ያሉ ሃገር በቀል እውቀት በመባል የሚታወቁት እንደ ሸክላ ስራና የእደጥበብ ውጤቶች በርካታ መሆናቸውን ገልጸው ፤ እንደዚህ አይነት በልምድ የሚሰሩ እውቀቶችን ለማስፋት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል ።
በተለይም የአሰራር ሂደታቸው ለትውልድ እንዲተላለፍ የመመዝገብ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ የሚናገሩት ባለሙያው ከሌሎች የአለም ሃገራት ልምድ በመውሰድ በቀጣይ ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ በሚኼድባቸው ሁኔታዎች በልምድ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ለማሳተፍ ሰንዶ ማስቀመጡ ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረው ፤ በተሰማሩበት የስራ መስክ ተቀባይነትን እንዲያገኙ የሚሰጡ መመዘኛዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም አመላክተዋል ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር አንዷለም ጎሹ ፤ በልምድ የተገኙ እውቀቶች ለሃገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳላቸው ገልጸው ፤ እንደ ኢትዮጲያ ያሉ ታዳጊ ሃገሮች በመደበኛ ትምህርት ከሚገኙ እውቀቶች ይልቅ በአብዛኛው በልምድ የተገኙ እውቀቶች ሰፊውን ቦታ የሚይዝ መሆኑን አመላክተዋል ።
በሃገር ደረጃ ያለው የሰው ሃይል ከፍተኛ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው ፤ በተለይም በልምድ እውቀት የዳበረው የሰው ሃይል በገጠርም ሆነ በከተማ ከፍተኛ ቁጥር እንዳለው ተናግረው ፤ በልምድ የካበተውን እውቀት እውቅና መስጠት ለሃገር የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል ።
በአብዛኛው በሃገራችን ያለው ከመደበኛ ትምህርት ውጪ የተገኘ የስራ ልምድ እምብዛም እውቅና ያልተሰጠው ነው የሚሉት ዶ/ር አንዷለም በየሴክተሩ በተደረጉ ጥናቶች ቀጣሪዎች የሚቸገሩት ከዩኒቨርስቲ በዘርፉ ሰልጥነው የሚወጡ ተማሪዎች በቂ የስራ ልምድ የሌላቸው በመሆናቸው ነውም ይላሉ። በስራ ላይ የሚገኘው እውቀት ካለው ፋይዳ አንጻር እውቅና በመስጠት ያላቸውን ጠቀሜታ ማጉላት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ።
ሰዎች በየትኛውም የሞያ መስክ በልምድ ያገኙትን እውቀት ህጋዊ ለማድረግ ወይም እውቅና እንዲኖረው ለማስቻል በየትኛውም የብቃት መመዘኛ ተቋማት ሄደው መመዘን የሚችሉበትን መመሪያ የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል መናገራቸው ይታወሳል ።
በልምድ እና በውርስ የተገኙ እውቀቶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና እውቅና በመስጠት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚቻል በሎም በኢትዮጵያ ያልተመሰከረላቸው በርካታ ባለሙያዎች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ፤
በልምድ እና በውርስ የተገኙ እውቀቶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና እውቅና በመስጠት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚቻል ተናግረው በሚቀጥሉት አመታትም እውቅና የመስጠት ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስተርዋ ካሁን ቀደም መግለጻቸው ይታወሳል ።
በስራና ከህሎት ሚኒስቴር በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ላይ የሙያ ደረጃ የስራተ ስልጠናና ብቃት ምዘና መሪ ስራ አስፈጻሚዋ ማስተዋል ወልዴ እንደገለጹት ፤ ዜጎች በተለያየ መንገድ በልምድና በውርስ በማግኘት እየሰሩበት ያለውን እውቀት ህጋዊ እውቅና እንዲያገኙ ለማስቻል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መመርያው መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።
የሃገር በቀል እውቀቶችን ጨምሮ በየትኛውም የስራ ዘርፍ በልምድ የተገኘ እውቀትን እውቅና ለመስጠት በወጣው መመሪያ መሰረት ዜጎች በልምድ እየሰሩ ባሉበት የስራ መስክ ላይ ለመመዘን ባላቸው ፍላጎት መሰረት የመመዘንና እውቅና የመስጠት ሰራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ። አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የምዘናው ተጠቃሚ እየሆኑ የሚገኙት የምህንድስናና የግብርናው ዘርፍ ላይ መሆኑን ገልጸው ፤ በ2017 ዓም ወደ 27 ሺ የሚጠጉ ተመዛኞች ምዘናውን በመውሰድ 24 ሺ ያህሉ ብቁ ሆነው መገኘታቸውን አብራርተዋል ።

የእውቅና መስፈርቱን ያሟሉና ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች ለሚሰማሩበት የስራ መስክ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚዋ ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በልምድና በውርስ የተገኙ እውቀቶችን በምዘና በቁ የሚያደርገውን መመሪያ በክልሎችም ላሉ ባለሙያዎችም ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረው ፤ በምዘና ብቃታቸውን ያረጋገጡ ባለሙያዎችን ቅድሚያ የስራ እድል የመስጠት አሰራር መኖሩን አብራርተዋል ።
የስራና ከህሎት ሚኒስቴር ያዘጋጀውን የምዘና እውቅና አሰራር በመጠቀም አሁን በስራላይ የሚገኙት አቶ አስቻለው ሞላልኝ እንደተናገሩት ፤ በአናጢነት ሙያ መስክ ለ 35 አመታት በልምድ መስራታቸውን ይገልጻሉ ። የምዘናና የውቅና መመሪያውን በመጠቀም በአናጢነቱ ብቻ ይሰሩ ከነበረው የስራ ዘርፍ ተጨማሪ ሞያ ማዳበራቸውን አብራርተዋል ።
ከስራ ምዘናው በመነሳት ሌሎች በልምድ የሚሰሩ ባለሙያዎችን በማገዝም ላይ እንደሚገኙ ተናግረው ፤ ምዘናውን በመውሰዳቸው ካገኙት ተጨማሪ እውቀት ባለፈ ፤ የደሞዝ እድገና በስራ ቅጥር ዙሪያ ቅድሚያ ማግኘት መቻላቸውንም ተናግረዋል ።
ሌላኛው በልምድ ባገኙት የስራ መስክ እውቅና አግኝተው እየሰሩ የሚገኙት አቶ ይሁን አበራ እንደገለጹት ፤ በኮንስትራክሽን የስራ ዘርፍ ላይ ያላቸውን ፍላጎት በልምድ በማዳበር በፍጥነት ስራውን መልመዳቸውን ገልጸው ፤ የስራ ልምዳቸውን በምዘና በማረጋገጣቸው የተሻለ ቦታ ላይ መሆናቸውንና ሌሎች ባለሙያዎች በቦታው ባይኖሩ እንኳን የነሱን ቦታ በሃላፊነት ተክቶ ለመስራት ብቁ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል ።
በርካታ ሃገር በቀል እውቀቶች ያሉዋቸው ባለሙያዎችን በማደራጀት ሲሰራ በሚታወቀው የሃገር ጥበብ ማደራጃ ድርጅት የስራና ፍይናንስ ሃላፊ አቶ ዋሴ ብርሃኑ ፤ በተቋሙ በርካታ ባለሙያዎች መኖራቸውን በመግለጽ አሁን ላይ ድርጅቱ በኮሪደር ግንባታ መነሳቱንና ሰራተኛው መበተኑን ገልጸዋል ።
ተቋሙ ራሱን ችሎ በምዘና ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት አለመቻሉን ገልጸው ፤ በተለያዩ ሃገር በቀል እውቀቶች የካበቱ ባለሙያዎች ቢኖሩም ፤ የስራና ከህሎት ያመቻቸውን በልምድ የተገኘውን እውቀት በምዘና የማዳበር አሰራር ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን ያብራራሉ ። በተለይም በተቋሙ ያሉ ባለሙያዎች አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው በልምድ ያላቸውን እውቀት በምዘና አረጋግጦ ሌላ የቅጥር አማራጭ ለማግኘት እንደሚገድባቸውም ነው ሃላፊው የሚገልጹት ።
በኢትዮጲያ ኢንጂነሪንግ ኮፖሬሽን ኮንስትራክሽን ዘርፍ አሰልጣኟ ጸገነት በላይ ፤ ኮፖሬሽኑ እየሰራቸው ካሉ በርካታ ስራዎች አንዱ ፤ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በልምድ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎችን የማሰልጠን እንዲሁም ምዘና የማዘጋጀት ስራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል ።
በዚህም በዘርፉ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን ከማፍራት አንጻር ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የሚገልጹት አሰልጣኟ ፤ ባለፉት 2 አመታት ወደ 10ሺ 85 የሚጠጉ ባለሙያዎችን በምዘና ብቁ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ። በተለይም በልምድ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ተጨማሪ ስልጠና የመስጠት ስራ በመስራት እገዛና ደጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል ።
ኢትዮጵያዊያን ከእናት ከአባቶቻቸው መደበኛ ባልሆነ መንገድ ያገኙትን እውቀት ጥቅም ላይ እንዲያውሉት ለማድረግ የተጀመረው ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው በርካታ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል ።
በልምድ የተገኙ ሃገር በቀል እውቀቶችን ለማስፋትና በምዘና በተረጋገጠ መልኩ ሰፊ የስራ እድል ማግኘት እንዲችሉ ከማድረግ አንጻር ያሉ ክፍተቶች በመኖራቸው የሚመለከታቸው አካላት በልዩ ትኩረት ሊሰሩበት እንደሚገባ በዳሰሳው የተመላከተ ሃሳብ ነው ።
በአስናቀች መላኩ
ምላሽ ይስጡ