ጥቅምት 04 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው 14ኛው የኢትዮ የዶሮ እርባታ ኤክስፖ (ETHIOPEX) እና 10ኛው የአፍሪካ የእንስሳት እርባታ ኤግዚብሽንና ኮንግረስ (ALEC) ከሰሞኑ ሊካሄዱ ነው።
በዘንድሮው ዝግጅት የእንስሳት መኖን፣ የእንስሳት ጤናን፣ ዶሮ እርባታን፣ ወተት፣ ስጋ፣ እንቁላል፣ አሳ ሃብት፣ ንብ እርባታን እንዲሁም ባዮ ኢነርጂን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረገው ዓውደ-ርዕዩ ከጥቅምት 20 እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል።
ዝግጅቱ በፕራና ኢቨንትስና አጋሮቹ አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የቴክኖሎጂና ግብዓት አቅራቢዎችን ከሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት ጋር ለማገናኘት ያለመ ነው ተብሏል።
ዓውደ-ርዕዩ ከ14 ሀገራት የተውጣጡ ከ80 በላይ ዓለምቀፍ የቴክኖሎጂ እና ግብዓት አቅራቢዎች እንዲሁም ታዋቂ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የዘንድሮው ኤግዚብሽን ለአራት ተከታታይ ዓመታት በተሳታፊነት የዘለቀውን የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ፓቪሊዮን እና የብራዚል ኤምባሲን የሚያካትት ጠንካራ ተሳትፎ ይኖረዋል ተብሏል።
ኤግዚቢሽኑ ከዚህ በፊት በነበሩት መርሀ-ግብሮች የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ ልምድና ተሞክሮ በማጋራት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት በዘርፉ ዕድገት ላይ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።
ዓውደ-ርዕዩ ከ5ዐዐዐ በላይ የንግድ ጎብኚዎችን ከኢትዮጵያ፣ ከምስራቅ አፍሪካ እና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል ተብሏል።
በዘርፉ ላይ በሰፊው የሚያተኩሩት እነዚህ ዓውደ-ርዕዮች፣ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ከዘመናዊ የልማት ስልቶች ጋር በማጣመር የዶሮ እርባታ፣ ወተት፣ ስጋ፣ አሳ ሃብትና ንብ እርባታ ንዑስ ዘርፎች ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ወደፊት የወተት ምርት ከ6.9 ቢሊዮን ሊትር ወደ 11.7 ቢሊዮን ሊትር ማሳደግ፤የእንቁላል ምርት ከ3.2 ቢሊዮን ወደ 9.1 ቢሊዮን ማሳደግ፤ የዶሮ ስጋ ምርት ከ90,000 ሜትሪክ ቶን ወደ 296,000 ሜትሪክ ቶን ማሳደግ፤ የማር ምርት ከ147,000 ሜትሪክ ቶን ወደ 296,000 ሜትሪክ ቶን ማሳደግ ላይ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ