መስከረም 29 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የዓለም አእምሮ ጤና ቀን በየዓመቱ መስከረም 30 በዓለም አቀፍ ደረጃ “በድንገተኛ አደጋዎችና ሰብአዊ ቀውስ ወቅት የአእምሮ ጤና አገልግሎት ተደራሽነት” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል።
የአማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ዳይሬክተር ዶ/ር ክብሮም ሃይሌ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ ጤና ተጋላጭነት መኖሩን ተናግረዋል። በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከሦስት እስከ አምስት ሰዎች አንዱ በቀላልና በከባድ ለአእምሮ ሕመም ተጋላጭ ሊሆን እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ። በአጠቃላይ በአለማችን ካሉ ከፍተኛ የአእምሮ ሕመም ተጋላጮች መካከል 29 በመቶው ብቻ ሕክምና እንደሚያገኙ በጥናት መረጋገጡን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የአእምሮ ጤናን ማስጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተረጋገጠ የአእምሮ ሰላም ሲኖር፣ የተረጋጋ የሀገር ዕድገት እንደሚረጋገጥ አስረድተዋል። ይህን ለማሳካት የበርካታ ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። የአእምሮ ሕክምና ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆንም ጥበቃ እና የተጠናከረ አቅም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
እየተከበረ ያለውን የዓለም አእምሮ ጤና ቀን አስመልክቶ፣ የአማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከተለያዩ የመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችና ሌሎች ኃላፊዎች ጋር በመሆን ድንገተኛ የአእምሮ ጤና አገልግሎት ተደራሽነትና የማኅበረሰብ ግንዛቤ አሰጣጥን በሚመለከት የፓናል ውይይት አካሂዷል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ