መስከረም 29 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)በዓለም ላይ ከሚገኙ ማዕድናት 30 በመቶው፣ ሊታረስ ከሚችለው መሬት ደግሞ 60 በመቶው በአፍሪካ አህጉር የሚገኝ ሲሆን፣ በተጨማሪም ከፍተኛ የሰው ቁጥር ባለቤት ብትሆንም፣ ለአህጉራዊ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የምታበረክተው 3 በመቶ ብቻ መሆኑ ከያዘችው የተፈጥሮ ሀብት ጋር የማይመጣጠን መሆኑን የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ገልጸዋል።
አፍሪካ በኢኮኖሚ ጠንካራ መሠረት ላይ እንዳትቆም እና ራሷን እንዳትችል እያደረጋት ያለው አህጉሪቱ የምትሰበስበው ዝቅተኛ ግብር ነው የሚል መነሻ ያለውና አህጉሪቱን ከግብር ሥርዓት እንዴት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል የሚመረምረው የአፍሪካ ቲንክ ታንክ ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የአፍሪካ የአቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ጸሐፊ ማማዱ ቢቴ እንዳሉት፣ አህጉረ አፍሪካ ከአጠቃላይ ጥቅል ምርት የምታበረክተው አስተዋፅዖ ከሌሎች አህጉራት አንፃር ዝቅተኛ ሲሆን፣ ለዚህም አንዱ ምክንያት የሚሰበሰበው ግብር ዝቅተኛ መሆኑ ነው። በአፍሪካ በበርካታ ሀገራት የሚሰበሰበው ግብር ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ከ12 እስከ 14 በመቶ ይሸፍናል። በዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ያለው አማካይ ውጤት 14 በመቶ አካባቢ ሲሆን፣ በእስያ እና በላቲን አሜሪካ ካለው የ20 በመቶ ምጣኔ አንጻር ሲታይ የአፍሪካ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ዋና ጸሐፊው አህጉሪቱ በዚህ ረገድ መጠነ ሰፊ ችግር የሚታይባት መሆኑን አመላካች ነው ያሉት ሲሆን፣ ለጠንካራ የግብር አሰባሰብ ሂደት መጓደል ምክንያት የሆኑትም፡- የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ያልተደራጁ ተቋማት መዋቅር እና በመንግስትና በዜጎች መካከል ያለው የመተማመን ችግር መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የዓለም ሀገራት በሌሎች አገራት አቅም እንዳልገፉ የገለጹት አቶ ዛዲግ አብርሃ፣ አፍሪካም በራሷ አቅም ለማደግ የምታደርገው ጥረት የሉዓላዊነትና የብሔር-መንግሥት ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል። አህጉሪቱ ያላትን ሀብት ልክ ሳትጠቀም መቆየቷ ማብቃት አለበት ያሉት አቶ ዛዲግ፣ ሀብትን ለመጠቀም የጎደለን አቅም ሳይሆን ተነሳሽነት መሆኑን ገልጸዋል። ለአብነትም፣ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በራስ አቅም መገንባት መቻሉ፣ አህጉሪቱ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በራሷ አቅም መገንባትና ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል ዋና ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።
አፍሪካ ያላትን ሀብት ለአውሮፓውያን እድገት ስታበረክት መኖሯን የገለጹት አቶ ዛዲግ፣ ይህ መቀየር የሚችልበትን ሥርዓት የምንገነባበት ሰዓት አሁን ነው ብለዋል። ከእነዚህ ሥራዎች አንዱ ደግሞ አፍሪካውያን እርስ በእርስ የመነገድ አቅማቸውን ሙሉ በሙሉ መጠቀም መቻል ነው፤ ይህ ሥራ መጀመሩን ገልጸው፣ ነገር ግን እስካሁን በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።
መናኸሪያ ሬዲዮ ባቀረበው ጥያቄ፣ የአፍሪካ የነጻ ንግድ አሁን ላይ እያደገ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ዛዲግ፣ ከእነዚህ ጉባኤዎች የሚገኙት ሪፖርቶች እና ምክረ ሀሳቦች እርስ በእርስ ለመደገፍ የምናደርገውን ጥረት አጠናካሪ ናቸው ብለዋል።
እስከ ነገ አርብ በሚቀጥለው የአፍሪካ ቲንክ ታንክ ጉባኤ ላይ የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት የተገኙ ሲሆን፣ በጉባኤው ላይ አፍሪካ ያላትን ሀብት የሚመጥን ጥቅም ከግብር ሥርዓት እንዴት ማግኘት ትችላለች የሚለው ከብዙሃኑ ተሳታፊዎች ምክረ ሀሳብ የሚቀርብበት፣ የተሻለ ልምድ ያላቸዉ ሀገራት ደግሞ ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት መሆኑን የጉባኤው አዘጋጅ፣ የአፍሪካ የአቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ጸሐፊ ማማዱ ቢቴ ጠቁመዋል።


የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ