መስከረም 29 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የሳዑዲ ዓረቢያ የስፖርት እና የመዝናኛ ባለሥልጣን እንዲሁም ታዋቂው የቦክስ ፕሮሞተር ቱርኪ አል-ሼክ የእንግሊዙን ታላቅ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድን (Manchester United) ሽያጭ በተመለከተ ከፍተኛ ግምት የተሰጠው መረጃ አጋርተዋል።
ይህ ከፍተኛ ሳዑዲ ባለሥልጣን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፣ ክለቡን ለአዲስ ባለሀብት የማስተላለፍ ሂደት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አመልክተዋል።
አል-ሼክ በእንግሊዝኛ እና በአረብኛ ቋንቋ በለጠፉት ጽሑፍ፣ “ዛሬ የሰማሁት ምርጥ ዜና ማንቸስተር ዩናይትድ ለአዲስ ባለሀብት የሚሸጥበት ስምምነት አሁን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ከቀድሞዎቹ ባለቤቶች የተሻለ ይሁን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲል ጽፈዋል።
ይህ መልእክት የመጣው ሰር ጂም ራትክሊፍ ከክለቡ 27.7% ድርሻ ገዝተው የኳስ ነክ ጉዳዮችን ማስተዳደር ከጀመሩ ከጥቂት ወራት በኋላ በመሆኑ፣ በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል። ግለሰቡ ስለ አዲሱ ባለሀብት ማንነት ወይም ስለ ሽያጩ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፣ አስተያየታቸው ስለ ክለቡ የባለቤትነት ለውጥ ግምቶችን አባብሶታል።
ቱርኪ አል-ሼክ በቦክስ ዓለም በሚያዘጋጁት ትልልቅ ፍልሚያዎች የሚታወቁ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ስለ ማንቸስተር ዩናይትድ አስተዳደራዊ ጉዳዮች አስተያየቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል።
እስካሁን ድረስ የግሌዘር ቤተሰብ ሙሉ ድርሻቸውን ለመሸጥ እየተዘጋጁ ስለመሆናቸው ከክለቡ በኩል የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም፣ የሳዑዲ ባለሥልጣኑ የሰጡት ፍንጭ በቀያይ ሰይጣኖቹ ዙሪያ ያለውን የባለቤትነት ውዝግብ ዳግም አቀጣጥሎታል።
የዩናይትድ አብዛኛው ድርሻ ባለቤቶችና ክለቡን ለሁለት አስርት ዓመታት ያስተዳደሩት አሜሪካውያኑ ግሌዘሮች፣ በታኅሣሥ ወር 2023 ዓ.ም. 1.25 ቢሊዮን ፓውንድ በመቀበል ለአይኖስ ኬሚካል ግሩፕ ባለቤት ለሆነው ፔትሮኬሚካሊስት እንግሊዛዊው ቢሊየነር ሰር ጂም ራትክሊፍ 25 በመቶ አነስተኛ ድርሻ ባለቤትነት እንዲኖረው ማድረጋቸው አይዘነጋም።
የኳታር ስፖርት ኢንቨስትመንት (Qatar Sport Investment) ወይም ሼክ ጃሲም የሚመራው ተቋም ላለፉት ሁለት ዓመታት ማንቸስተር ዩናይትድን ለመግዛት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ