መስከረም 26 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ግብፅ በየጊዜው አጀንዳ እየቀያየረች ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የምታሳስተው፣ ኢትዮጵያ እና የተፋሰሱ አገራት በሕዳሴው ግድብ እና በአባይ ወንዝ በሰላማዊ መንገድ እንዳይጠቀሙ ለማድረግ እንደሆነ ምሁራን ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጸዋል።
በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ አበራ ሄጲሶ በሱዳን ለሚደርሰው የጎርፍ አደጋ ኢትዮጵያን ለመውቀስ መጀመሪያ ገለልተኛ አካል ጉዳዩን ሊመረምረው እንደሚገበ ገልጸው፤ በዚህ ፍጥነት ግብፅ ይህንን መረጃ የማጋራት መብት የላትም ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ድርቅ ሊፈጥር ይችላል ከሚል ውንጀላ ወደ ጎርፍ አደጋ ስጋት ተቀይሮ ኢትዮጵያን ለመተቸት መሞከር ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገራት ጋር የመነጠል እሳቤ እንጂ፣ የግድቡን የጥራት ደረጃ ካለመረዳት የመነጨ ነው ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡
ለዚህም ትልቁ ማሳያ ግብጽ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የማይታመን ክስ ማቅረቧን ይጠቅሳሉ፡፡
የውሃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው እና በሕዳሴው ግድብ ላይ ተደራዳሪ የነበሩት አቶ ፈቅ አሕመድ፣ በሕዳሴው ግድብ ላይ ያላትን አቋም በየጊዜው የምትቀያይረው ግብፅ፣ መሠረተ ቢስ ክሶችን ማቅረቧን አሁንም የምትቀጥልበት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን ጉዳዩን በሆደ ሰፊነት ማለፍ ይገባል ብለዋል።
ግብጽ የተፋሰሱ አገራት በፍትሐዊ መልኩ ሊጠቀሙት የሚገባውን የተፈጥሮ ሀብት በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎቷን ለማሳካት የምታደርገው አምባገነናዊ አካሄድ ኢትዮጵያን መውቀስ መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን የኢትዮጵያን ፍላጎት እና መብት ያላከበረ አካሄድ መቼም ቢሆን ተቀባይነት እንደማያገኝ አሳውቀዋል።
ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 80ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ግብፅ በርካታ ከእውነት የራቁ ክሶችን ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማቅረቧ የሚታወስ ነው።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ