መስከረም 26 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች በሚከበሩ የብሄር ብሄረሰቦች በዓላት ላይ አንዱ በሌላኛው ክብረ በዓል መታደሙ እንደ ሀገር ለታቀደው ሀገራዊ አንድነት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ከተለያዩ የሀገሪቷ አከባቢዎች በመምጣት በኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ የታደሙት ተሳታፊዎች ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮ የኢሬቻ ክብረ በዓል መስከረም 24 በአዲስ አበባ በሆረ ፊንፊኔ መስከረም 25/2025 ዓ.ም ደግሞ በደመቀ ሁኔታ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ መከበሩ ይታወቃል፡፡
በዓሉ ላይ ለመታደም ከተለያዩ የሀገሪቷ አከባቢዎች የመጡ ተሳታፊዎች አሁን ላይ በስፋት እየተስተዋለ ያለው አንዱ በሌላኛው ክብረ በዓል ላይ መታደሙ እንደ ሀገር ለታሰበው ሀገራዊ አንድነት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡
ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጡ የኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ አባቶች ልዑካን ቡድን አባል የሆኑት የወረዳው አስተዳደሪ አቶ ገዝኻኝ በራቆ የዘንድሮ የኢሬቻ ክብረ በዓል ብሄር ብሄረሰቦችን በማሰባሰብ አንድ ያደረገ እንደሆነ በማመላከት በተለይም ለትውውቅ ትልቅ መድረክን የፈጠረ በመሆኑ ይህ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የመጠው ወጣት አሸናፊ በለጠ በበኩሉ አሁን ላይ በተለያዩ አከባቢዎች የዘመን መለወጫ በዓላትን ጨምሮ በርካታ የአደባባይ ክብረ በዓልት እየተከበሩ እንደሚገኙና እሱ ከመጣበት አከባቢም ቶኪቢያ የሚባል የዘመን መለወጫ እንደሚከበር ተናግሯል፡፡
በበዓሉ ላይ በርካታ ታዳሚያን ከተለያዩ አከባቢዎች በመምጣት በጋራ እያከበሩ እንደሚገኙና ይህም ለሀገራዊ አንድነት ያለው ፋይዳ የጎላ ነው ብሏል፡፡
በቀጣይ ኢሬቻን ጨምሮ በተለያዩ አከባቢዎች የሚከበሩ የአደባባይ በዓላትን ሰላማዊ በሆነ መልኩ እሴቱን ጠብቆ በማክበር በአለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ማድረግ እንደሚገባ ታዳሚያኑ ገልጸዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ