መስከረም 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)ጃፓን የፀሐይን ኃይል ከምድር ምህዋር ላይ ያለገደብ አሰባስቦ በገመድ አልባ መንገድ ወደ ምድር የማስተላለፍ ታሪካዊ ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች መሆኑን አስታውቃለች። ይህ “ኦሂሳማ” (OHISAMA) የተሰኘው ፕሮጀክት፣ ታዳሽ ኃይልን የማምረት ቴክኖሎጂን ወደ አዲስ ምዕራፍ ሊያሸጋግር የሚችል ወሳኝ ምዕራፍ ተደርጎ ተቆጥሯል።
በጃፓን የጠፈር ሲስተምስ (Japan Space Systems) የሚመራው ይህ ተነሳሽነት፣ 2025 (እ.ኤ.አ) ሳያልቅ አንድ ትንሽ የሙከራ ሳተላይት ወደ ምህዋር በመላክ የፀሐይ ብርሃንን በፓነሎች አማካኝነት ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል ይለውጣል። ከዚያም ይህን ኃይል በ ማይክሮዌቭ ሞገዶች አማካኝነት ወደ ምድር የሚገኝ የመቀበያ ጣቢያ ለማስተላለፍ ያለመ ነው።
ሳተላይቱ መጀመሪያ ላይ ወደ ምድር የምታስተላልፈው ኃይል አንድ ኪሎዋት (1 kW) ገደማ ብቻ ነው። ይህም ለአንድ ትንሽ የቤት ውስጥ ዕቃ (እንደ ቡና ማሽን ወይም የእቃ ማጠቢያ) ለአንድ ሰዓት ያህል የሚበቃ ሲሆን፣ ዓላማው ለንግድ አገልግሎት የሚሆን ትልቅ ኃይል ማመንጨት ሳይሆን፣ ቴክኖሎጂው በተግባር እንደሚሰራ ማረጋገጥ (Proof of Concept) ነው።
የሙከራው ስኬት ወደፊት ትላልቅ ሳተላይቶችን በመጠቀም፣ ከምድር ገጽ የአየር ሁኔታ እና የሌሊት ዑደት ነጻ የሆነ፣ ቀጣይነት ያለው ንጹህ ኃይል የማመንጨት ራዕይ እንዲሳካ በር ይከፍታል።
ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ ጃፓን የዚህን ቴክኖሎጂ የሙከራ ገጽታዎች በማረጋገጥ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ነው። ይህ የህዋ ላይ የፀሐይ ኃይል ወደፊት የአለምን የኃይል ፍላጎት ለማሟላትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ