መስከረም 19 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) ዴንማርክ በኮፐንሃገን የሚካሄደውን የአውሮፓ ኅብረት (EU) መሪዎች ጉባኤ ምክንያት በማድረግ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሁሉም ሲቪል ድሮኖች በረራ ለአንድ ሳምንት ያህል መከልከሏን የሀገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህ እገዳ ተግባራዊ የተደረገው በአውሮፓ ጉባኤ ወቅት ደህንነትን ለማረጋገጥ ነው። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዴንማርክ አየር ማረፊያዎች እና ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ በተደጋጋሚ ያልታወቁ ድሮኖች መታየታቸው ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ከፈጠረ በኋላ ነው።
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ባወጡት መግለጫ፣ እገዳው ተግባራዊ የሚሆነው ከዛሬ ሰኞ እስከ ዓርብ ድረስ ሲሆን፣ ዓላማውም “የጠላት ድሮኖች ከህጋዊ ድሮኖች ጋር ተሳስተው ግራ መጋባት እንዳይፈጠር ለመከላከል” መሆኑን ገልጸዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፣ እገዳው ለፖሊስ እና ለሌሎች የጸጥታ አካላት ስራን ለማቀላጠፍ እና ትኩረታቸውን በጉባኤው ደህንነት ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ለማስቻል ታስቦ የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
እገዳውን የጣሰ ማንኛውም ሰው በገንዘብ ቅጣት ወይም እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል የዴንማርክ ባለስልጣናት አስጠንቅቀዋል። ወታደራዊ፣ ፖሊስ እና የድንገተኛ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ድሮኖች ግን ከዚህ እገዳ ነጻ መሆናቸው ተገልጿል።
ጉባኤው የአውሮፓ መሪዎች ስለ አውሮፓ መከላከያና ለዩክሬን ስለሚደረገው ድጋፍ ለመወያየት የሚገናኙበት ሲሆን፣ ዴንማርክ በቅርቡ በተፈጠሩት የድሮን ክስተቶች ሩሲያ ልትሳተፍ ትችላለች ብላ መጠቆሟ የሁኔታውን ክብደት አጉልቶታል። ሞስኮ ግን ይህንን ውንጀላ አስተባብላለች።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ