መስከረም 19 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) በ2030 ለአፍሪካ አገራት ከሚቀርቡ መድሐኒቶች ውስጥ 9.6 በመቶው የኢትዮጵያ ምርት እንዲሆን በስፋት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መድሐኒትና የህክምና መገልገያዎች አምራች ዘርፍ ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ተፈራ ለመናኸሪያ ሬዲዮ በሰጡት ቃል፣ ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብን ገንብታ ማጠናቀቅ እንደቻለች ሁሉ፣ በመድሐኒት ዘርፍም ዳግም ህዳሴን መፍጠር እንደሚኖርባት አሳውቀዋል።
ማህበሩ ከተቋቋመ 22 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል። ዶክተር ታደሰ አክለውም፣ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገራት መድሐኒት የመላክ አቅሟን ማሳደግ ካልቻለች፣ አሁንም ሸማች ሆና እንደምትቀር አስጠንቅቀዋል።
ባለፉት 60 ዓመታት የመድሐኒት ማምረቻ ተቋማት መገንባት መቻሉን ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ምንም እንኳ የአፍሪካ አገራት ተጠቃሚ የሆኑ ቢሆንም፣ በተቋቋሙበት ዓላማ ልክ ወደፊት መውጣት ያልቻሉ፣ አሁን ላይ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑና የተዘጉ ፋብሪካዎች እንዳሉ ገልጸዋል።
አሁንም ድረስ የመድሐኒት ግብዓት የሚያመርቱ ተቋማት ውስን በመሆናቸው፣ ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አሳስበዋል። ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት አንጻር ከፍተኛ መጠን ያለው መድሐኒት ማምረት እንደሚጠበቅባትም ጠቁመው፣ የ9.6 በመቶውን የገበያ ድርሻ ለማሳካት ከወዲሁ በስፋት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ለአፍሪካ አገራት ተደራሽ የምታደርጋቸው መድሐኒቶች ለተላላፊ እና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እንዲሁም በዕድሜ ልክ የሚወሰዱ መድሐኒቶችን ያካተቱ ይሆናሉ።
በተለይም ለስኳር፣ ለደም ግፊት እና ለአእምሮ ሕመም ማስታገሻነት የሚውሉ መድሐኒቶችን የማምረት አቅም እንዳለ እና ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለአፍሪካ አገራት ለማዳረስ ጥረት እንደሚደረግ ዶክተር ታደሰ ተፈራ አብራርተዋል።
ማህበሩ ከሰሞኑ 22ኛውን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄዱ ይታወሳል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ