መስከረም 14 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ)የአሜሪካ ጦር በውጊያ አውድ ውስጥ የፀሐይ ኃይልን መጠቀም መጀመሩ ተገለጸ። ወታደሮች አሁን በዩኒፎርማቸው፣ ቀሚስና ሌሎች እቃዎች ውስጥ የተገነቡ ተንቀሳቃሽ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎችን በመሞከር ላይ ሲሆኑ፣ ይህም በማንኛውም ቦታ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቻቸውን ኃይል መሙላት ያስችላቸዋል።
ይህ ፈጠራ ወታደሮች ከዚህ ቀደም ይዘዋቸው የሚንቀሳቀሱትን ከ10 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝኑ ተጨማሪ ባትሪዎችን ከጀርባቸው ላይ ማንሳት ያስችላል። ይህም የጦር ሰራዊቱን የመንቀሳቀስ አቅም ከመጨመር ባሻገር፣ ለአደጋ የሚያጋልጠውን የሎጅስቲክስ ድጋፍ ጥገኝነት ይቀንሳል።
እነዚህ የፀሐይ ኃይል ፓነሎች እንደ ጂፒኤስ መሳሪያዎች፤ ሬዲዮዎችና ዳሳሾች (sensors)፤ የሌሊት መመልከቻ መነጽሮች (night-vision goggles)፤ የሰውነት ካሜራዎች እና ዳታ ማስተላለፊያዎች የመሳሰሉ ወሳኝ መሳሪያዎችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ኃይል ያመነጫሉ ተብሏል።
የአሜሪካ ጦር ዘመናዊነት ቡድኖች እና የመከላከያ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ይህንን ፈጠራ በበረሃዎች፣ በደን እና በሩቅ ደሴቶች ላይ በሚገኙ የውጊያ ማዕከሎች ውስጥ በመሞከር ላይ ናቸው። ተለዋዋጭ፣ ቀላል ክብደት ያላቸው እና ዘላቂነት ያላቸው እነዚህ የፀሐይ ጨርቆች በከፋ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ውጤታማ ሆነው መገኘታቸው ተገልጿል።
የዚህ ፈጠራ ዋና ጠቀሜታ በጦርነት ጊዜ የኃይል አቅርቦት ትልቅ ተጋላጭነት መሆኑን ማስወገድ ነው። ለውሃ እና ለምግብ ኃይልን ወደ ጦር ግንባር ማጓጓዝ አደጋን የሚፈጥርና ውስብስብ የሎጂስቲክስ ሰንሰለት የሚፈልግ ጉዳይ ሲሆን፣ የፀሐይ ኃይልን መጠቀም ግን ይህንን ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል። በዚህም ወታደሮች የበለጠ ነጻነትና ደህንነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ሲሆን፣ ከዘላቂ የኃይል ምንጮች ጋርም የሚጣጣም ነው።
በመሆኑም ፀሐይ የሀብት ምንጭ ብቻ ሳትሆን፣ አሁን ደግሞ በጦርነት ስልት ውስጥ ትልቅ ስልታዊ ጠቀሜታን አግኝታለች።
ምላሽ ይስጡ