መስከረም 14 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ)በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ ምስራቅ በለሳ ወረዳ የሚገኘው የሙት አንሳ ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም መነኮሳትን ለመርዳት በማኅበራዊ ሚዲያ የተጀመረው የገቢ ማሰባሰብ ዘመቻ ወደ 30 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉን የገዳሙ አባቶች አስታወቁ።
ዛሬ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ አባቶች እስካሁን 29,750,000 ብር በጥሬ ገንዘብ እንዲሁም 6,208,810 ብር የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የገዳሙ ቄሰ ገበዝ አባ ብርሃነ ሰላም ሙሃባው እንደተናገሩት፣ የተሰበሰበው ገንዘብ ለተለያዩ የልማት ስራዎች ውሏል። ከእነዚህም መካከል፤ ገዳሙን ለመድረስ አስቸጋሪ የነበረው 179 ሜትር ርዝመት ያለው ተራራ ተቦርቡሮ እና በአርማታ ደረጃ ተሰርቷል።
ለገዳማውያኑ ትምህርት ቤት፣ የማምረቻ ሼድ፣ የሴት ገዳማውያን መኖሪያ ቤት እና የቤተ ክርስቲያን ግንባታዎች ተከናውነዋል። በተጨማሪም፣ በአካባቢው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመኖሩ በሶላር ኃይል እንዲበራ ተደርጓል ተብሏል።
ገዳሙ ድርቅ በሚበዛበት አካባቢ በመሆኑ፣ በተሰሩት የመልካምድር ስራዎች አማካኝነት የምግብ ዋስትናው በተወሰነ መልኩ ተሻሽሏል።
አባቶች በቀጣይ ለሚሰሩ የልማት ስራዎች 210 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ለዚህም፣ በሀሙሲት ከተማ 30,000 ካሬ ሜትር ቦታ ከመንግስት በሊዝ ተረክበዋል፤ በዚህም ላይ የአብነት ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ እና ሌሎች ህንጻዎች ለመገንባት አቅደዋል።
የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻውን ለማጠናከርም፣ ጥቅምት 16 ቀን 2018 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ “ገዳማዊ ልማት ለቤተ ክርስቲያን ትሩፋት” በሚል መሪ ቃል ትልቅ ጉባኤ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። በዚህ ጉባኤ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም፣ በገዳሙ የተጀመሩት የልማት ስራዎች በአካባቢው ባለው የሰላም እጦት እና የግንባታ እቃዎች ዋጋ መናር ምክንያት እየተስተጓጎሉ መሆኑም ተገልጿል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ