መስከረም 14 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) በጃፓን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሶስት ዓመታት፣ የትምህርት ስርዓቱ ከፈተና ውጤት ይልቅ ለተማሪዎች ስነ-ምግባር፣ ባህሪና ማህበራዊ እሴቶች ቅድሚያ ይሰጣል። ይህ አሰራር አጠቃላይ ስብዕናን በመገንባት ላይ ያተኮረ መሆኑን የሀገሪቱ የትምህርት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በጃፓን የመጀመሪያ ክፍል ተማሪዎች ስለ አክብሮት፣ የሌሎችን ስሜት መረዳት (empathy)፣ኃላፊነት መውሰድ እና ሌሎች ማኅበራዊ እሴቶችን ይማራሉ። የትምህርት ቤቱ መርህ ልጆች አካዳሚክ ትምህርቶችን ከመጀመራቸው በፊት ጠንካራ ማኅበራዊ እና ስነ-ምግባራዊ መሰረት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ለዚህም ማሳያ ተማሪዎች የራሳቸውን ክፍል እና ትምህርት ቤት እንዲያፀዱ ይደረጋል። ይህም ተግሣጽንና የጋራ ኃላፊነት ስሜትን ለመገንባት እንደሚያግዝ ይታመናል።
የትምህርት ባለሙያዎች እንደሚያብራሩት፣ ይህ አቀራረብ ከቁጥርና ከፊደል በፊት ስሜታዊ ብልህነትን (emotional intelligence) እና ጥሩ ባህሪን ቅድሚያ ይሰጣል። ይህም ሁሉን አቀፍ እና ለማህበራዊ ህይወት ዝግጁ የሆኑ ዜጎችን ለመፍጠር ያስችላል ተብሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የጃፓን የትምህርት ስርዓት ተማሪዎችን በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በባህሪም ጭምር የሚያንጽ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እያገኘ ነው ተብሏል፡፡
ምላሽ ይስጡ