መስከረም 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ ላይ ከመስከረም 3-11 ተካሂዶ ፍጻሜውን አግኝቷል። በውድድሩ ሀገራችን ኢትዮጵያ በ36 አትሌቶች ከ800 ሜትር አንስቶ እስከ ማራቶን ድረስ በተለያዩ ርቀቶች ብትካፈልም፣ በ4 ሜዳሊያ ብቻ በአግራሞት ሳይሆን በአስደንጋጭ ሁኔታ እጅን በአፍ የሚያስጭን ውጤት ተመዝግቦበት ፍጻሜውን አግኝቷል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በ2 ብር እና በ2 ነሐስ በድምሩ በ4 ሜዳሊያዎች ውድድሩን የቋጨች ሲሆን፣ ከ34 ዓመታት በኋላ በመድረኩ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ሳትችል ከአለም 21ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ወትሮ በመካከለኛና ረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ ወርቅ በቀላሉ በጀግኖች አትሌቶቻችን የሚመዘገብበት ሁኔታ በተደጋጋሚ የታየ፤ በታሪክም የተመዘገበ ወርቃማ ክስተቶች ባለቤት የሆኑ አትሌቶች በትውልድ ቅብብል ያንን በተደጋጋሚ ሲያሳዩን ቆይተዋል።
አሁን ግን አሰልጣኞች እና አትሌቶች ከፌዴሬሽኑ የሚሰጡ መመሪያዎችን አለመከተል፣ ለሀገር ውድድር ራስን ብቁ ከማድረግ ይልቅ በግል ውድድሮቻቸው ላይ ጠንክሮ መታየት፣ ልዑክ ቡድኑ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሌለው መሆኑ፣ እንዲሁም በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር ሀገርን ለመወከል ሄደው የቡድን ስራ ለመስራት ዝግጁ ያልሆኑ አትሌቶች የተንጸባረቁበት የውድድር ምዕራፍ ሆኖ አልፏል።
ጎረቤት ሀገር ኬንያ 7 ወርቅ፣ 2 ብር እንዲሁም 2 ነሐስ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የአፍሪካ አንደኛ ስትሆን፣ ከአለማችን ደግሞ አሜሪካን በመከተል ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
እንደ ባህል ስፖርታችን የሚታየው፣ የማንነት እና የክብር መገለጫችን የሆነው አትሌቲክሳችን በእግር ኳሱ መንገድ ተቃኝቶ በውጤት እጦት ከመታመስ በጊዜ መታደግ እንደሚያስፈልግ መሰመር ያለበት ነጥብ ነው።
የሀገራችን የአትሌቲክስ ሁኔታ በደንብ መፈተሽ እንዳለበት ጥቆማ የሰጠው የቶኪዮ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ ይበልጥ በምንታወቅባቸው የመካከለኛና የረጅም ርቀት ሩጫዎች ላይ ከዘላቂ ተቀናቃኞቻችን ኬንያውያን ባሻገር የምዕራብያኑ እና የአውሮፓውያኑ አትሌቶችም ሜዳሊያ ያገኙባቸው የውድድር ምዕራፎች መሆናቸው በትልቁ ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በግልጽ ያመላክታል።
በሚካኤል ደጀኔ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ