መስከረም 09 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት የሃገር ውስጥና የውጭ ሸቀጦችን የምልልስ ሂደት ለማሳለጥ የአዋጭነት ጥናት አድርጎ ወደ ኢንቨስትመንት ሊገባ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በተያዘው 2018 ዓ/ም በባቡር እና መርከብ አገልግሎት ዘርፍ ተጨማሪ የአዋጭነት ጥናት አድርጎ 200 ቢሊዮን ብር የመመስረቻ ካፒታል መመደቡን የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በየነ ኢብራሂም ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አገልግሎቱ በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ማቀዱን ገልጸው፤ ከዚህም ውስጥ ከኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር በመነጋገር አዲስ የማጓጓዣ ባቡሮችን ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የሸቀጦች የምልልስ ሂደትን ለማሳለጥ እንደሚሰራ ነው ያመላከቱት፡፡ በተያዘው የበጀት አመትም 9 አዳዲስ መርከቦችን ለመግዛት እንደታቀደ ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከውጪ የሚገዙ እቃዎችን ከጅቡቲ ወደብ በመነሳት ወደ አገሪቱ ከተሞች ለማጓጓዝ የሚያገለግሉ 570 ከባድ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ወደ 1ሺህ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱ የየብስና የባህር የትራንስፖርት ተደራሽነት እና ስፋትን ማሳደጉ ከወደብ እስከ መሃል ከተሞች ያለውን የምልልስ ጊዜ እንደሚሳልጥ፤ በዚህም የሃገር ውስጥ ምርትን ወደ ውጭ እንዲሁም የውጭ ምርትን ደግሞ ወደ ሃገር ውስጥ በሚፈለገው ጊዜ ለማጓጓዝ እንደሚረዳ አመላክተዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ