መስከረም 06 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ከጷጉሜ 1 እስከ ጷጉሜ 5 ድረስ የሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ እና የሁለተኛው የካረቢያን እና አፍሪካ መሪዎች (ካሪኮም) ጉባኤን ማካሄዷ ይታወሳል፡፡
በጉባኤው እንዲሁም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምርቃት ስነ-ስርዓት ለመታደም የሀገራት መሪዎች እና ሌሎችም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች የተገኙበት በመሆኑ ሆቴሎች ከቅድመ ዝግጅት እስከ ጉባዔው ፍፃሜ ድረስ ጥራት ያለው መስተንግዶ መስጠታቸውን ለጣቢያችን የገለፁት የሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ናቸው፡፡
በመዲናዋ የሚከናወኑ ሁነቶች የሆቴል ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያነቃቁ መሆኑን በመጥቀስ በጉባዔዎቹ ለመታደም ከመጡ ተሳታፊዎች አንፃር በርካታ ሆቴሎች እንግዶቹን ማስተናገድ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
ጉባኤዎቹ ተጀምረው እስከሚጠናቀቁ ድረስ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውኑ ከነበሩ ተቋማት ጋር ውይይት እና ግምገማ እንደሚኖር በመጥቀስ፤ ማህበሩም ለሆቴል ባለንብረቶች ግምገማውን በማሳወቅ በቀጣይ የሚኖሩ መሰል ፕሮግራሞችን ለማስተናገድ እራሳቸውን እንዲያበቁ እንደሚረዳ አንስተዋል፡፡
በተያዘው የበጀት ዓመት የሚከናወኑ ትልልቅ ዝግጅቶችን በማህበሩ ስር ያሉ ሁሉም ሆቴሎች ማስተናገድ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰሩ እንዲሁም በሆቴሎቹ ስር ለሚገኙ ሰራተኞች የአገልግሎት አሰጣጥ ስልጠና ለመስጠት ማህበሩ ማቀዱንም አስታውቀዋል፡፡
በሆቴሎች የሚሰጡ አገልግሎቶች ሀገርን ከማስተዋወቅ አንፃር ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን አቅም እንዲያጎለብቱ ማህበሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ