መስከረም 05 ቀን (መናኸሪያ ሬዲዮ) ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ በአትላንቲክ ውቅያኖስ በሁለቱም በኩል የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎችን ግንባታ የሚያፋጥን ታሪካዊ ስምምነት ለመፈራረም መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። ይህ ስምምነት “ለላቀ የኑክሌር ኃይል የአትላንቲክ አጋርነት” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ የፕሮጀክት ፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱን ከ3-4 ዓመታት ወደ ሁለት ዓመት ለማሳጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የሁለቱ ሀገራት ስምምነት ዋነኛ ዓላማ ከካርቦን ነፃ ወደሆነ የኃይል ምንጭ የሚደረገውን ሽግግር ማፋጠን፣ የኢኮኖሚ እድገትን ማሳደግ እና በቅሪተ አካል ነዳጅ ገበያ ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ ነው። ስምምነቱ በእንግሊዝ እና በአሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የስራ እድሎችን እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል።
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር፣ ይህ ስምምነት ቤቶችን ኃይል መስጠት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውን፣ ማህበረሰቦችን እና የሁለቱን ሀገራት ምኞትም የሚያንቀሳቅስ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ፣ በርካታ አሜሪካውያን እና እንግሊዛውያን ኩባንያዎች በእንግሊዝ ውስጥ የኑክሌር ኃይል ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ የንግድ ስምምነቶችን ይፋ አድርገዋል። ከእነዚህም መካከል በሃርትልፑል እስከ 12 የሚደርሱ የላቀ ሞጁል ሬአክተሮችን ለመገንባት የተደረገው ስምምነት ተጠቃሽ ነው።
በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት በ2028 መጨረሻ ድረስ በሩሲያ የኑክሌር ቁሳቁስ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለማስወገድ ቃል ገብተዋል። ይህም የኃይል ደህንነትን ለማጠናከር እና የሩሲያን ተጽዕኖ ለመቀነስ ያለመ ነው። ትብብሩ በኑክሌር ውህደት ምርምር ላይም የሚዘልቅ ሲሆን፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እውቀት እና የላቁ የሙከራ ተቋማትን በመጠቀም ወደ ንግድ የሚውል የውህደት ኃይል ለማምረት የሚያስችል ጥናቶችን ያካትታል።
ስምምነቱ በዚህ ሳምንት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእንግሊዝ በሚያደርጉት የመንግሥት ጉብኝት ወቅት እንደሚፈረም ይጠበቃል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ