ነሐሴ 27 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ባለፉት 6 ዓመታት የጳጉሜ ወር ቀናት ስያሜ ተሰጥቶት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር የቆየ ሲሆን፣ የ2017 ዓ.ም የጳጉሜ ቀናትን ስያሜ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል።
በዚህም ጳጉሜ አንድ፡ የፅናት ቀን የተባለ ሲሆን ጽኑ መሰረት ብርቱ ሃገር በሚል መሪ ቃል በፅናት የተሻገርናቸውን የሀገር ችግሮች በማሰብ የሚከበር መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ አስታውቀዋል።
በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚሰሩ ወታደሮች፣ ለአርሶ አደሮች፣ ለተማሪዎች እና መምህራን እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በፅናት የተሻገሯቸውን ችግሮች ለማሰብ የሚከበር ሲሆን በቀጣይ የሚጠብቁንን ሀገራዊ ችግሮች በፅናት በአንድነት ለመሻገር የሚታሰብበት ቀን ነው ብለዋል።
ጳጉሜ ሁለት፡ የሕብር ቀን የተባለ ሲሆን “ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ይሆናል ያሉት ሚንስትሩ፣ በሀገር ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ እና ባህላዊ ቅርሶቻችን እንዲሁም የብዝሃ ሕይወት ማዕከል እንደመሆናችን፣ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እና የወል ትርክታችንን ለማፅናት ነው ብለዋል። የፖለቲካ ስብራትን ለመጠገን፣ የነጠላ ትርክትና የጥላቻ አካሄድን በማደብዘዝ ህብረታችንን የምናፀናበት ሲሆን ቀኑ ሲከበርም የበጎ አድራጎት ስራዎች የሚከናወኑበት፣ ችግር ላይ ያሉትን የመርዳትና ድጋፍ ለሚፈልጉ ሁሉ ማዕድ የማጋራት ስራዎች የሚሰሩበት እንደሚሆን ተገልጿል።
ጳጉሜ ሶስት፡ የእመርታ ቀን በሚል የተሰየመ ሲሆን “እመርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል፣ በዚህ ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን በመመዘንና በማስቀጠል ታስቦ የሚከበር ቀን መሆኑን ሚኒስትሩ የገለጹት ሲሆን ሁሉም በየደረጃው የሚያከብረው ይሆናልም ብለዋል።
ጳጉሜ አራት፡ የማንሰራራት ቀን ሲሆን “ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ይሆናል ያሉት ሚንስትሩ በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ የመካከለኛ ዘመን ላይ የነበሩት ዕቅዶች የተጀመሩበትና የተጠናቀቁበት ዓመት በመሆኑ ነው ብለዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተጠናቀቀበት፣ የተሟላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተጀመረበትና የተለያዩ የሀገር ውስጥ ፕሮጀክቶች የተጀመሩበት ብሎም የተጀመሩት ደግሞ የተጠናቀቁበት ዓመት እንደነበር አብራርተዋል።
የመጨረሻው ጳጉሜ አምስት፡ የነገው ቀን በሚል ስያሜ “ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር የስታወቁ ሲሆን በተለይም በዲጂታል ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት በማሰብ በአዲሱ ዓመትም ለማስቀጠል የሚከበር መሆኑን ነው ዶክተር ለገሰ ቱሉ ያብራሩት።
የዘንድሮ ዓመት የጷግሜ ቀናትን ከፌደራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ መዋቅር በሁሉም ደረጃዎች እንደሚከበር የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አመላክቷል።
በኢቫን ስለሺ
ምላሽ ይስጡ