ነሐሴ 27 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ዘርፉ አሁንም በቂ የሰው ሀይል ስለሌለው ክፍተቶቹን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቬየሽን ባለስልጣን በዛሬው እለት ለአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ ሚና መወጣት የሚችሉ 114 ተማሪዎችን በማሰልጠን ማስመረቁን ነው የገለጸው።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ንጉሴ ሰልጣኞች ያለ ምንም ድካም እና ቸልተኝነት ስልጠናውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል። ሰልጣኞቹ ከንድፈ ሀሳብ ትምህርት ባለፈ የተግባር ላይ ልምምድ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ በዘርፉ ይህን ያህል መጠን ያለው ሰልጣኝ ተቀብሎ እንደማያውቅ እና በዘርፉ ያለውን የሰው ሐይል እጥረት ለመፍታት እንደሚረዳው ገልጿል።
ሰልጣኞች ወደ ስራ ሲገቡ የአየር ክፍሉን ደህንነት ማረጋገጥ እና ማስጠበቅ የሚችሉበትን አቋም ይገነባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተገለጸው።
ዘርፉን አሁንም በእውቀት እና ክህሎት መምራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ባለሙያዎችን ማሰልጠን እንደተቻለም አስታውቀዋል፡፡
ስልጠናው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በርካታ አካላትን ጨምሮ ተቋማት ሚናቸው ከፍተኛ እንደነበረም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ የአቬሽኑን ዘርፍ ማሳደግ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመው፤ በተለይም ለዘርፉ ማደግ ቀዳሚውን ስፍራ የሚዘውን ተቋም በሰው ሀይል እና ቴክኖሎጂ ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁንም እየገነባቻቸው ያሉ ፕሮጀክቶችን ደህንነት ለመፈተሽ እና አስተማማኝ ለማድረግ የአቬሽኑ ዘርፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአቬየሽኑ ዘርፉ ከተመሰረተ 80 አመታት ማስቆጠሩ የሚታወቅ ነው።
በእየሩስ ፈጠነ
ምላሽ ይስጡ