ነሐሴ 27 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በሱዳን ምዕራባዊ ዳርፉር ክልል ውስጥ በመራ ተራሮች አካባቢ ታራሲን በተባለች መንደር ላይ በደረሰ ከባድ የመሬት መንሸራተት ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን በስፍራው የሚንቀሳቀሰው አማጺ ቡድን አስታወቀ።
የሱዳን ነጻ አውጪ ንቅናቄ/ሠራዊት (SLM/A) ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ አደጋው የተከሰተው ባለፈው እሁድ ለብዙ ቀናት ከዘነበ ከባድ ዝናብ በኋላ ሲሆን፣ መንደሯ ሙሉ በሙሉ በተንሸራታች መሬት ተሸፍናለች ብለዋል።
ቡድኑ በመግለጫው እንዳለው፣ ባጋጠመው አደጋ ከመንደሩ ነዋሪዎች መካከል አንድ ሰው ብቻ መትረፍ የቻለ ሲሆን፣ ሌሎች ከ1,000 በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው አልፏል ተብሏል።
አማጺ ቡድኑ አስከሬኖችን ለማውጣት እንዲቻል የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች በአስቸኳይ ወደ ስፍራው እንዲደርሱ ጥሪ አቅርቧል።
አደጋው የደረሰበት አካባቢ አሁንም ድረስ በሱዳን የመንግስት ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ የድጋፍ ሰራዊት (RSF) መካከል በሚካሄደው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ለሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ለመድረስ አስቸጋሪ ከሆኑ ቦታዎች አንዱ መሆኑ ተዘግቧል።
ምላሽ ይስጡ