ነሐሴ 23 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)አየርላንድ የእንስሳት እርባታን እና የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ከፍ ያለ ትኩረት በመስጠት ትታወቃለች። ከዚህም አንዱ የላሞች ልዩ መታወቂያ ሥርዓት ነው። በአየርላንድ ውስጥ የምትገኝ እያንዳንዷ ላም “የላም ፓስፖርት” የሚል ልዩ ሰነድ ይሰጣታል ተብሏል።
ይህ ፓስፖርት ተራ ሰነድ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ ላሟ ሁሉን አቀፍ መረጃ ይዟል ተብሏል። ከእነዚህም መካከል፡-
👉የመለያ ቁጥር (ID Number)፡ እያንዳንዱ ላም የራሱ የሆነ ልዩ መለያ ቁጥር አለው።
👉የልደት ቀንና ቦታ፡ ላሟ የተወለደችበት ትክክለኛ ቀንና ቦታ በሰነዱ ላይ ይሰፍራል።
👉የቤተሰብ ታሪክ (Family Lineage)፡ የላሟን እናትና ሌሎች የዘር ሐረግ ዝርዝሮች ያካትታል ነው የተባለው ።
ይህ ሥርዓት አውሮፓ ሕብረት ባወጣው ህግ የሚመራ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም አንድ እንስሳ ከተወለደበት እርሻ አንስቶ እስከ ገበያ ወይም እርድ ቦታ ድረስ ያለውን ሙሉ ጉዞ መከታተል ነው። ይህ ደግሞ በምግብ ደህንነት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።
ስርዓቱ የበሽታ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ፣ ተጠቃሚዎች የሥጋውን ምንጭና ታሪክ ሙሉ በሙሉ እንዲያምኑ ያደርጋል። ስለዚህም በአየርላንድ የላሞች ፓስፖርት ለምግብ ጥራትና ደህንነት ወሳኝ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ተብሏል።
ምላሽ ይስጡ