ነሐሴ 23 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የእስራኤል ጦር በየመን ዋና ከተማ በሆነችው ሳና ላይ ባደረሰው የአየር ጥቃት የኢራን ደጋፊ የሆነውን የሁቲ ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸውን የየመን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። የሁቲ ቡድን በበኩሉ ይህንን ዘገባ በይፋ አስተባብሏል።
ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት፣ ጥቃቱ የተፈጸመው የሁቲ ከፍተኛ የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮች በሚገኙበት አንድ የመኖሪያ ህንጻ ላይ ነው። በርካታ የየመን ሚዲያዎች እና አንዳንድ የእስራኤል ባለስልጣናት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ አል-ራሃዊ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በጥቃቱ መሞታቸውን መግለጻቸውን ዘገባዎች ጠቁመዋል።
ሆኖም የሁቲ የፖለቲካ ቢሮ ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ ይህ መረጃ ትክክል አይደለም እና እስራኤል የውሸት ወሬዎችን በማሰራጨት ላይ ትገኛለች ብለዋል። ጥቃቱ በርካታ ሲቪል ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ አንዳንድ የመሠረተ ልማት አውታሮችም መመታታቸውን አስታውቀዋል።
ይህ የአየር ጥቃት እስራኤል ላይ በተደጋጋሚ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ለቆዩት ሁቲዎች የተሰጠ ምላሽ መሆኑን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል። ውጥረቱ እየጨመረ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች በተለያዩ ግንባሮች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን እንደሚያባብሱ እየዛቱ ይገኛሉ።
ምላሽ ይስጡ