ነሐሴ 23 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ያለ ምክንያት ደጋግመው የሚደውሉ የስልክ መስመሮችን የሚያግድ አሰራር መዘርጋቱን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
በቀን ከ3ሺህ እስከ 4ሺህ አላስፈላጊ ስልኮችን እንቀበል ነበር የሚሉን የኮሚሽኑ የአይ ሲቲ ዳይሬክተር ፈትለወርቅ ግዛው፤ በተደጋጋሚ የሚደወሉ ስልኮችን የሚያግድ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡
በትንሹ ከአምስት ጊዜ በላይ ያለጉዳይ የሚደወሉ የስልክ መስመሮችን ለተወሰነ ጊዜ እንደሚታገዱ ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ የታገዱት ቁጥሮች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከእግድ እንደሚወጡ እንዲሁም አዲሱ አሰራር አንድ ሰው ከየት አካባቢ ሆኖ እንደሚደውል እስከ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ሙሉ መረጃን እንደሚያሳይ ገልፀዋል፡፡
ከፍተኛ የሆነው ሃሰተኛ የስልክ ደውል ከአዲስ አበባ ውጪ የሚደወል መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሯ፤ ከአዲስ አበባ ውጪ ያለ የስልክ ጥሪ ወደ 939 እንዳይገባና አገልግሎቱ በሌሎች መደበኛ መስመሮች እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ ኮሚሽኑ በአንድ ጊዜ 15 የስልክ ጥሪዎችን መቀበል እንደሚችል እና በስልክ መስመሩ የእሳት አደጋን፤ ወላድንና ታካሚን ጨምሮ አስከ አስር ትክከለኛ ጥሪዎች እንደሚያስተናገድ አንስተዋል፡፡
አጭር የስልክ መስመሩ ለወላድ እናቶች፤ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ታካሚዎች እና ለድንገተኛ አደጋ የሚያገለግል በመሆኑ አላስፈላጊ ጥሪዎች የሚያከናውኑ ዜጎች ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ የኮሚሽኑ የአይ ሲቲ ዳይሬክተር ፈትለወርቅ ግዛው አሳስበዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ