ነሐሴ 20 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የፌዴራል ሪዘርቭ ባንክ ገዢ የሆኑትን ሊሳ ኩክን በሞርጌጅ ማጭበርበር ወንጀል ከስልጣናቸው ማውረዳቸውን አስታወቁ። ይህ ድንገተኛ ውሳኔ የአሜሪካን ማዕከላዊ ባንክ ነጻነትን በሚመለከት ትልቅ የህግ ክርክር እንደሚያስነሳ ተገልጿል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ውሳኔያቸውን ሰኞ አመሻሽ ላይ በትሩዝ ሶሻል (Truth Social) ማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ በለጠፉት ደብዳቤ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ላይ ኩክ ‘አታላይ እና ወንጀል ሊሆን የሚችል ባህሪ’ አሳይተዋል ሲሉ ወንጅለዋቸዋል። በደብዳቤያቸው ላይ “የአሜሪካ ህዝብ እና እኔም በታማኝነትዎ ላይ እምነት ሊኖረን አይችልም” ሲሉ በመግለጽ፣ ከስልጣን ለማንሳት ‘በቂ ምክንያት’ እንዳለኝ ወስኛለሁ ብለዋል።
በፌዴራል ሪዘርቭ ቦርድ ውስጥ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት የሆኑት ኩክ ላይ የቀረበው ክስ የመጣው በትራምፕ የተሾሙትና የፌዴራል የቤቶች ፋይናንስ ኤጀንሲ (Federal Housing Finance Agency) ኃላፊ የሆኑት ቢል ፑልቴ ነው። ፑልቴ የፍትህ ሚኒስቴር እንዲያጣራ የጠየቁት ክስ እንደሚለው፣ ኩክ በ2021 ሁለት ቤቶችን፣ አንዱን ሚቺጋን ሌላውን ደግሞ አትላንታ ውስጥ፣ ዋና መኖሪያዬ በማለት ለብድር አመቺ ሁኔታዎችን አግኝተዋል። ይህ ደግሞ የሞርጌጅ ማጭበርበር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ፑልቴ ተናግረዋል።
ይህ ውሳኔ የብዙዎችን ትችት አስከትሏል። የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የፌዴራል ሪዘርቭ ህግ ገዢን ከስልጣን ማውረድ የሚፈቀደው ‘በምክንያት’ (for cause) ብቻ ነው። ይህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በቦታ ላይ ለሚፈጸም ከባድ ስህተት ወይም የኃላፊነት ጉድለት ሲሆን፣ የፕሬዝደንት ትራምፕ እርምጃ ግን ከቦርድ አባልነት በፊት በነበረ ህይወት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ህጋዊነት ላይ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ኩክ በ2022 በፕሬዝደንት ጆ ባይደን የተሾሙ ሲሆን፣ የስራ ዘመናቸውም እስከ 2038 የሚዘልቅ ነበር ተብሏል።
በመግለጫ የሰጡት ኩክ በበኩላቸው፣ ፕሬዝደንት ትራምፕ እሳቸውን ከስልጣን የማውረድ ‘ህጋዊ ስልጣን’ እንደሌላቸው ገልጸዋል። “በማስፈራራት ከቦታዬ ለመልቀቅ ፍላጎት የለኝም” ብለው፣ “የአሜሪካን ኢኮኖሚ ለመርዳት የጀመርኩትን ስራ እቀጥላለሁ” ሲሉ አክለዋል።
ትራምፕ የፌዴራል ሪዘርቭ ነጻነት ላይ ጫና ለማሳደር የሚያደርጉት ጥረት አካል ተደርጎ የሚታየው ይህ እርምጃ፣ በገንዘብ ገበያ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ። ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት የሚመራ ሲሆን፣ የህግ ሂደቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ኩክ በቦታቸው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ