ነሐሴ 20 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስራኤል በሶሪያ ግዛት ውስጥ በቅርቡ ያደረገችውን ወረራ በጽኑ አውግዟል። ሚኒስቴሩ ይህ የእስራኤል ድርጊት የሶሪያን ሉዓላዊነትና ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ መሆኑን ገልጿል።
በዛሬው ዕለት የወጣው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ እንዳመለከተው፣ የእስራኤል ጥቃት በሶሪያ እና በእስራኤል መካከል በ1974 ዓ.ም. የተፈረመውን የድንበር ማቋረጥ የሌለበት ስምምነት (Disengagement Agreement) የሚጥስ ነው ብሏል።
መግለጫው አክሎም ሳውዲ አረቢያ የሶሪያ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ለማስጠበቅ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች እንደምትደግፍ ገልጿል። ይህም የሁለቱ አገራት የቅርብ ጊዜ ግንኙነት መሻሻልን ተከትሎ የመጣ ሲሆን፣ ሳውዲ አረቢያ ለሶሪያ ሙሉ ድጋፍ እንደምትሰጥ የሚያሳይ ነው።
በተያያዘ ዜና፣ የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስራኤል በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ሄርሞን ተራራ አካባቢ ወታደሮቿን በማስገባት ግዛቱን ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረጓን ከሷታል። የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ምንም አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ነው የተባለው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ሶሪያ ከበርካታ ዓመታት አለመግባባት በኋላ በቅርብ ጊዜ የዲፕሎማሲያዊ እና የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ መሆናቸው ይታወቃል።
የሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተናገረው ይህ የቅርብ ጊዜ መግለጫ የሳውዲን ለሶሪያ ያላትን ጠንካራ አቋም የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ