👉ዝንቦቹ የሰዎችን እዳሪ በመብላት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሚሞቱ ናቸው ተብሏል።
ነሐሴ 20 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የዓለምን የቆሻሻ ችግር ለመፍታት ሳይንቲስቶች በዘረመል የተቀየሩ “ሱፐር ዝንቦችን” እየፈጠሩ መሆናቸውን አዲስ ጥናት አመለከተ። ይህ ሳይንስ ልቦለድ አይደለም፣ ይልቁንም በአውስትራሊያ የሚገኙ ተመራማሪዎች እየሰሩበት ያለ አዲስ እና ተስፋ ሰጪ መፍትሄ ነው ተብሏል።
የጥናቱ ዓላማም የተለያዩ ኦርጋኒክ ቆሻሻዎችን በብቃት መብላትና ማበስበስ የሚችሉ ዝንቦችን መፍጠር ነው ተብሏል። ቀድሞውንም ቆሻሻን ለማስተዳደር ሲያገለግሉ የነበሩ እንደ ጥቁር ወታደር ዝንቦች (black soldier flies) ያሉ ነፍሳትን የተፈጥሮ ችሎታ በመጠቀም፣ ሳይንቲስቶች በዘላቂነት ላይ የተመሰረተ የቆሻሻ አወጋገድ አዲስ ዘመን እየከፈቱ መሆኑ ተመላክቷል።
እነዚህ በዘረመል የተቀየሩ ነፍሳት ቆሻሻን የምንይዝበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ ሊለውጡት ይችላሉ የተባለ ሲሆን ከተለመዱት የቆሻሻ አወጋገድ ዘዴዎች በበለጠ ፍጥነትና ሙሉ በሙሉ ቆሻሻን ማስተናገድ እንዲችሉ ሊቀየሩ ይችላሉ ተብሏል።
ከዚህም በላይ፣ የዚህ ሂደት ውጤቶች ንጹህ ፕላኔት መፍጠር ብቻ አይደለም። ዝንቦቹ እራሳቸው ወደ ጠቃሚ ሀብቶች ሊለወጡ ይችላሉ። የእነሱ ባዮማስ (አካል) እንደ ከፍተኛ ፕሮቲን ያለው የእንስሳት መኖ፣ የባዮፊውል እና ሌሎች ጠቃሚ ኬሚካሎችን ለማምረት ሊያገለግል ይችላል ነው የተባለው።
ይህ አዲስ ግኝት ትንሽ ነፍሳት ቆሻሻችንን ወደ ጠቃሚ ሀብት ለመለወጥ ቁልፍ እንደሆኑ ያሳያል፤ ይህም እውነተኛ “ክብ ኢኮኖሚ” (circular economy) እና ለሁሉም ንጹህ የወደፊት ጊዜን ሊፈጥር እንደሚችል ተመላክቷል።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ