ነሐሴ 19 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የትምህርት ሥልጠና ባለስልጣን በአዲስ አበባ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመስከረም 08 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 08 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ባደረገው ማጣራትና ግምገማ መሰረት የዳግም ምዘገባ ያሟሉ የትምህርት ተቋማት 75 እንደሆኑና 112 ካምፓሶች ፤556 ፕሮግራሞች ለመስክ ምልከታ ብቁ እንዳልሆኑ መረጋገጡም ተመላክቷል፡፡
ባለስልጣኑ የግምገማ መሰፈርቶቹን ካሻሻለ በኋላም ቢሆን የ3 ተቋማት 3 ካምፓሶች 17 ፕሮግራሞች ፍቃዳቸው ሲጸና 25 ተቋማት 37 ካምፓስ 146 ፕሮግራም የሚጠበቅባቸዉን ያላሟሉና በስድስት ወራት እንዲያሟሉ የተባሉ መሆናቸዉ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም 62 ተቋማት 66 ካምፓሶች ፤ 256 ፕሮግራሞች ደግሞ ግምገማውን ያላሟሉ ፈቃዳቸው የተነጠቁ በመዲናዋ አዲስ አበባ የሚገኙ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መሆናቸውን ተቋማቱ በተገኙበት ይፋ አድርጓል፡፡
ይህን መነሻ በማድረግ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በግል ከፍተኛ ተቋማት ላይ የተገኘዉ ዉጤት እጅግ አስደንጋጭና ሪፖርቱ ባለፉት አመታት እንደሀገር በሰርዓተ ትምህርቱ የደረሰንበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም የትምህርት ጥራት ሲጓደል በሀገር ደረጃ ሊመጣ የሚችለው የተረዳን ይመስለኛል፤ይህ አይነቱ ግምገማ በቀጣይ በመንግስት ትምህርት ቤቶችም ይቀጥላል ሲሉ አክለዋል፡፡
ከፍተኛ የግል የትምህርት ተቋማቱ ሰብሰብ ብለው በጋራ በመደራጀት ጠንካራ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንዲመሰርቱም የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ምክረ ሃባቸውን አጠናክረዋል፡፡
በተጨማሪም ትምህርት ላይ ያልመሰረትነው ትውልድ ነገ ሀገርን ያጠፋል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ስድስት ወራት እንዲያሻሽሉ የተሰጣቸውን ማሻሻያ በማያደርጉ ተቋማት ላይ ህጋዊ ርምጃዎች እንደሚወሰዱና የትምህርት ጉዳይ እንዲሁ የሚታለፈ እንዳማይሆን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
በደጀኔ እሸቱ
ምላሽ ይስጡ