ነሐሴ 20 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በኢንዶኔዥያ የኤሴህ ግዛት የሚገኝ አንድ እስላማዊ ፍርድ ቤት፣ ሁለት ወንዶች ልጆችን በህዝብ ፊት እንዲገረፉ ፈረደባቸው። እነዚህ ወጣት ወንዶች በፍርድ ቤቱ አባባል “መተቃቀፍና መሳሳም” በሚል የግብረ ሥጋ ግንኙነት ወንጀል ተከሰው ነው።
የኢንዶኔዥያ ፍርድ ቤት የከሰሳቸው ወንዶች እርስ በርሳቸው ሲሳሳሙ እና ሲተቃቀፉ በመያዛቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
የ20 እና 21 ዓመት የሆናቸው ሁለቱ ወንዶች፣ በባንዳ አቼ ከተማ በሚገኝ የህዝብ መናፈሻ መጸዳጃ ቤት ውስጥ፣ ነዋሪዎች ባደረጉት ጥቆማ በሃይማኖታዊ ፖሊሶች ተይዘዋል።
የኤሴህ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ይህ ድርጊት ወደ “የተከለከሉ ወሲባዊ ግንኙነቶች” ሊያመራ የሚችል ነው በማለት እያንዳንዳቸው ለ80 ጊዜ በጅራፍ እንዲገረፉ ወስኗል።
ይህ ቅጣት በዋና ከተማይቱ በባንዳ አቼ ውስጥ ባለ አንድ መድረክ ላይ፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ፊት በይፋ ተፈጽሟል። ፍርዱ የተሰጠው ሌሎች ስምንት ሰዎች በዝሙትና በቁማር ወንጀል ተከሰው ከተገረፉ በኋላ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይህንን ቅጣት በጽኑ አውግዘውታል። ድርጅቶቹ እንደገለጹት፣ ቅጣቱ የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ደንቦችን የሚጥስ እና ተቀባይነት የሌለው “ጭካኔ የተሞላበት” ድርጊት ነው ብለዋል።
ኤሴህ በሙስሊም አብላጫ ከሚኖራት ኢንዶኔዥያ ግዛቶች መካከል ሸሪዓ ህግን የምትተገብር ብቸኛዋ ግዛት መሆኗ ይታወቃል።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ