ነሐሴ 19 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) አንድ የ13 አመት ታዳጊ ሶስት እሽግ ጥሬ ፈጣን ኑድል ከተመገበ በኋላ ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ በግብፅ የምግብ ደህንነት እና የልጆች የአመጋገብ ልምዶች ላይ አሳሳቢ ጉዳዮች ተነስተዋል። አደጋው አገሪቱን ያናወጠ ሲሆን ብዙዎችን ለኑድል እና ለሌሎች ፈጣን ምግቦች ያለውን አመለካከት እንዲመረምሩ አድርጓል።
ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ሃምዛ የተባለው ወጣት ፈጣን ምግቡን ከበላ ከ30 ደቂቃ በኋላ ማስታወክ፣ ላብ እና ከባድ የሆድ ህመም ምልክቶች ታይተውበታል። ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም፣ እርዳታ ሳይደርስለት በአምቡላንስ ውስጥ ህይወቱ አልፏል።
የግብፅ ባለሥልጣናት አደጋውን ተከትሎ ምርመራ መጀመራቸውን ገልጸዋል፤ ኑድሉን የሸጠው ሱቅ ባለቤት በቁጥጥር ስር ውሏል፣ የኑድል ምርቱ ደግሞ መርዛማነት ወይም ብክለት ስለመኖሩ እየተመረመረ ነው። ሆኖም፣ የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ውጤቶች ምርቱ ከመደበኛ መስፈርቶች ጋር የሚጣጣም መሆኑን ያመለክታሉ። ይህም የሃምዛ ሞት በብዛትና በጥሬው በተበላው ኑድል ምክንያት በደረሰ የአንጀት መዘጋት ወይም ሌሎች ከባድ የጤና ችግሮች ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።
የጤና ባለሙያዎች ፈጣን ኑድል በከፍተኛ መጠን ሶዲየም፣ እና እንደ Tertiary-Butyl Hydroquinone ባሉ አርቲፊሻል ንጥረ ነገሮች የበለፀገ መሆኑን ያስጠነቅቃሉ። እነዚህ ንጥረ ነገሮች በተበስለ ሁኔታ በአጠቃላይ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንደሆነ ቢታሰብም፣ ጥሬ ኑድል መመገብ የሰውነትን የአንጀት ሂደት ሊጎዳ እንደሚችል እና የጤና ስጋትን ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ይህ አሳዛኝ ክስተት በግብፅ ውስጥ ወላጆች ስለልጆቻቸው የአመጋገብ ልምዶች የበለጠ እንዲያስቡ እና የፈጣን ምግቦች አደጋ ላይ ግንዛቤ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ባለሙያዎች ፈጣን ምግቦችን ሁልጊዜ ከማሸጊያው ላይ ባለው መመሪያ መሰረት ማብሰል እንደሚገባ እና በተለይም ለልጆች ስለትክክለኛ አመጋገብ ማስተማር ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።
በጌታሁን አስናቀ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ