ነሐሴ 17 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ቬትናም የትራፊክ ፍሰትን እና የህግ ጥሰቶችን ለመቆጣጠር በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ ካሜራዎችን ለመትከል በዝግጅት ላይ መሆኗ ተገለጸ።
ይህ እርምጃ በሀገሪቱ መንገዶች ላይ የነበሩትን የሰው ፖሊስ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በቴክኖሎጂ ለመተካት ያለመ ነው ተብሏል።
የቬትናም መንግስት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፣ አዲሶቹ የኤ.አይ. ካሜራዎች የትራፊክ ጥሰቶችን እንደ ፍጥነት ገደብ ማለፍ፣ ቀይ መብራት ማለፍ እና ትክክለኛ ያልሆነ መንገድ መጠቀምን በመሳሰሉ ድርጊቶች ላይ ወዲያውኑ ምላሽ መስጠት ይችላሉ ተብሏል።
እነዚህ ካሜራዎች ከማዕከላዊ የቁጥጥር ስርዓት ጋር የተገናኙ ሲሆን፣ ጥሰት ፈጻሚዎችን በቅጽበት በመለየት ቅጣት እንዲጣልባቸው መረጃውን የሚያስተላልፉ ይሆናል ነው የተባለው።
ይህ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የትራፊክ ቁጥጥርን ይበልጥ ቀልጣፋ እና ውጤታማ እንደሚያደርገው የሚጠበቅ ሲሆን፣ የሰው የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እና ሙስናን ሊቀንስ እንደሚችል ይታመናል ነው የተባለው።
በአንዳንድ የሀገሪቱ ከተሞች የሙከራ ትግበራዎች መጀመራቸውን የሀኖይ ከተማ ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል።
የቬትናም የትራፊክ ስርዓት በከፍተኛ የሞተር ሳይክል ብዛት እና የህዝብ ብዛት ምክንያት ፈታኝ እንደሆነ ይነገራል።
በመሆኑም ይህ አዲስ የኤ.አይ. ቴክኖሎጂ ትግበራ፣ የትራፊክ አደጋዎችን እና የመንገድ መጨናነቅን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ