ነሐሴ 19 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኖርዌይ ኩባንያ በሆነው በዴሰርት ኮንትሮል (Desert Control) የተገኘ አዲስ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በረሃማ አሸዋን በሰባት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ወደ ለም አፈር መለወጥ መቻሉ ተዘግቧል። ይህ ፈጠራ በደረቅ አካባቢዎች የሚገኙ መሬቶችን ለማልማት እና የግብርና ምርትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጭቃ የሚባል ንጥረ ነገር በአሸዋ ላይ በመርጨት የሚሰራ ነው የተባለ ሲሆን የዚህ ፈሳሽ ጭቃ ቅንጣቶች ከአሸዋው ቅንጣቶች ጋር በመጣበቅ ውሃና ንጥረ ነገሮችን የመያዝ አቅም ያለውን የአፈር መዋቅር ይፈጥራሉ ተብሏል። ይህም አፈሩ ውሃን እንዳያፈስ እና እፅዋት የሚፈልጓቸውን ንጥረ ነገሮች እንዲይዝ ያስችላል ነው የተባለው።
የዚህ ቴክኖሎጂ ትልቁ ጠቀሜታ የመስኖ ውሃ ፍላጎትን እስከ 50 በመቶ መቀነሱ ነው የተባለ ሲሆን ይህ ደግሞ በውሃ እጥረት በሚሰቃዩ የዓለማችን ክፍሎች ለግብርና ልማት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በተጨማሪም፣ ቴክኖሎጂው የምድረ በዳ መስፋፋትን በመከላከል የአካባቢ ጥበቃን ይደግፋል ነው የተባለው።
በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የተደረጉ ቀደምት ሙከራዎች እንደሚያሳዩት፣ ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተለያዩ ሰብሎችንና ዛፎችን ማብቀል ተችሏል። ይህም ባድማ የሆኑ መሬቶችን ወደ አምራች መሬት በመቀየር ለምግብ ዋስትና መሻሻል ወሳኝ መሆኑን ያመለክታል።
ይህ አዲስ የኖርዌይ ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ በረሃማ አካባቢዎችን ወደ አርሻ መሬትነት በመቀየር የምግብ ምርትን ለማሳደግ እና የሰዎችን ህይወት ለማሻሻል የሚያስችል ተስፋ ሰጪ መፍትሄ ሆኖ ቀርቧል።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ