ነሐሴ 19 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ከወላጅነት መብት እና ቀለብ አወሳሰን ጋር በተያያዘ ጉዳያቸው በፍ/ቤት የሚታይ ህጻናት ሙሉ መብታቸው የተጠበቀ እንዲሆን በወጣው መመሪያ የኢ- መደበኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውን ወላጆች ገቢ ለማወቅ ፈታኝ መሆኑ ታዉቋል፡፡
ከወላጅነት መብት እና ቀለብ አወሳሰን ጋር በተያያዘ ጉዳያቸው በፍ/ቤት የሚታይ ህጻናት ሙሉ መብታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል በሚል በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዘጋጀቱ ካሁን ቀደም መገለፁን ተከትሎ መናኸሪያ ሬዲዮ ያለውን አፈፃፀም በተመለከተ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን አነጋግሯል።
መመሪያው ከ ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓም. ጀምሮ ወደስራ መግባቱንና አሁንም በስራ ላይ መሆኑን የገለጹት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ተክለሃይማኖት ዳኘው ፤ ኢትዮጵያ የህጻናት መብቶችን በተመለከተ ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ስምምነቶችን ብታጸድቅም ሁሉም መብቶቻቸው በህግና መመሪያ ተደግፈው እየተተገበሩ እንዳልነበር አስታዉሰዋል፡፡
በተለይም ወላጆች በፍቺ ሲለያዩ ህጻናት በህግ የተደነገገላቸውን ቀለብ የማግኘት መብት ለመወሰን ጉዳዩን የሚያዩ ዳኞች በጉዳዩ ላይ የተሰናዳ መመሪያ እንዲሁም ዝርዝር ነገር ባለመኖሩ ለአሰራር አመቺ እንዳልነበር ገልጸዋል ። በዚህም ወላጆቻቸው በፍቺ የተለያዩ ህጻናት ቀለብ የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅና አስፈላጊውን እንክብካቤ ሁኔታ ለማስጠበቅ ውሳኔ ለመስጠት እያገዘ መሆኑንና ውጤታማ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለ ህጻናቱ የቀለብ አወሳሰን እንዲያግዝ በሚደረገው የወላጆቹን የገቢ ሁኔታ የማጣራት ሂደት በተለይ የኢ- መደበኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው ወላጆችን ገቢ ለማጣራት ፈታኝ እየሆነባቸው መሆኑና በየጊዜው እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት ስራው ላይ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል ።
መመሪያው በቀጣይ ምን ምን ነገሮች ሊሻሻሉበት ይገባል የሚለውን በተመለከተ ጥናቶችን ለማድረግ እቅድ ተይዟል ብለዋል።
በአስናቀች መላኩ
ምላሽ ይስጡ