ነሐሴ 18 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በቅርቡ ባደረጉት አስገራሚ ጥናት፣ 500 ቻትቦቶችን (AI ሮቦቶችን) ያሳተፈ የማኅበራዊ ሚዲያ ሙከራ ፍፃሜው ግጭት መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
ተመራማሪዎቹ 500 ቻትቦቶችን በመጠቀም ቀላል የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ ፈጥረው ባደረጉት ሙከራ፣ ቦቶቹ በየትኛውም አልጎሪዝም እና ማስታወቂያ ግፊት ሳይደረግባቸው በራሳቸው ወደየአመለካከታቸው መከፋፈላቸውን አረጋግጠዋል ተብሏል።
ለቦቶቹ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም፣ ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸውን ተጠቃሚዎች በመከተል በራሳቸውን የአስተሳሰብ መዋቅር ፈጥረዋል ነው የተባለው።
በዚህም ምክንያት፣ ቦቶቹ የሚያገኟቸው መረጃዎች የየራሳቸውን አመለካከት የሚያጠናክሩ ብቻ ሆነዋል ነው የተባለው።
በጥናቱ ወቅት፣ በጣም ግጭት ቀስቃሽ እና የተጋነኑ መልዕክቶች ከሌሎች ይልቅ ከፍተኛ ተወዳጅነት እና ዳግም መጋራት (reposts) አግኝተዋል ተብሏል። ይህም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚታየውን አነጋጋሪ እና ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶች በሰፊው የመሰራጨት ዝንባሌን የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ተመራማሪዎቹ ፖላራይዜሽንን ለመቀነስ በተለምዶ የሚነሱ መፍትሄዎችን ሞክረዋል የተባለ ሲሆን እነዚህም ልጥፎችን በጊዜ ቅደም ተከተል ማሳየት፣ የላይክ እና ሼር ቁጥሮችን መደበቅ እንዲሁም ተቃራኒ አመለካከቶችን ማስተዋወቅ ናቸው።
ይሁን እንጂ፣ ከእነዚህ ጣልቃ ገብነቶች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ የቦቶቹን ፖላራይዜሽን ከ6% በላይ መቀነስ አልቻሉም ተብሏል።
በዚህም ሁሉም ሮቦቶች በመጨረሻም እርስ በርሳቸው ጦርነት ቀስቅሰዋል ነው የተባለው።
ይህ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የማህበራዊ ሚዲያ ችግር ከአልጎሪዝሞች ወይም ማስታወቂያዎች ባለፈ በመድረኮቹ መዋቅራዊ አሰራር ውስጥ የተደበቀ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ምንም እንኳን ጥናቱ ሰው ሰራሽ የማሰብ ችሎታ ቦቶችን ቢጠቀምም፣ ግኝቶቹ ግን ጤናማ እና የተለያዩ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩባቸው ማህበራዊ መድረኮችን ለመፍጠር ያለውን ፈታኝ ሁኔታ የሚያሳዩ ናቸው ተብሏል።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ