ነሐሴ 14 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ) የአስራ አንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ጥምረቱ ወደ ውህደትም የሚያድግ መሆኑ ተገልጿል።
አሁን ላይ በጋራ ለመስራት ያለመ ጥምረት ቢሆንም በቅርቡ ጥምረቱ ወደ አንድ ፓርቲ አድጎ ሊዋሃድ እንደሚችል የጥምረቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዳሮት ጉማ ተናግረዋል።
በመጪው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫም ጥምረቱ በአንድ ምልትክ ነው የሚወዳደረው የሚሉት ሰብሳቢው ይህም በቅርቡ የፓርቲዎቹን ጥምረት ወደ አንድ አላማ አዋህዶ አንድ ፓርቲ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ገልጸዋል። አስራ አንዱ ፓርቲዎች እስከተስማሙ ድረስ አንድ ግንባር እስከመፍጠር ነው የጥምረቱ አላማ ሲሉም የኮሚቴው ሰብሳቢ ተናግረዋል። ለየብቻ ሆኖ ተጽእኖ መፍጠር አልተቻለም በሚል ወደ መጣመር ያደገው የፓርቲዎቹ ግንኙነት ለፖለቲካ ምህዳሩ አስተዋጾ ለማድረግ ከጥምረት እስከ ውህደት ያሉት ሂደቶች በቅንነት እንዲካሄዱም እንሰራለን ብለዋል።
ምንም እንኳን የጥምረቱ ኮሚቴ ሰብሳቢ ውህደቱ በቅርቡ እንደሚፈጠርና የጥምረቱ አላማ አንድ ፓርቲ እስከመሆን ድረስ ነው ቢሉም ውስጣዊ የፖለቲካ ልዩነትና የፓርቲዎች የተለያየ ፍልስፍና ሂደቱን ቀላል እንደማያደርገው የጥምረቱ አንድ አካል የሆነው ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ተናግሯል።
አሁን ባለው ሁኔታ አብሮ ለመስራት በሚል ጥምረቱ መከናወኑን እንጂ ወደ ውህደት ስለማደጉ ሌሎች ውይይቶችና እንደ ፓርቲ በቂ ስምምነቶች ሊኖሩ ይገባል ሲሉ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አቶ ጽጋቡ ቆፓ ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል። አላማችን በጋራ የመታገል እንጂ ቀዳሚው ጉዳይ ውህደቱ አይደለም በማለትም ለጊዜው እንደ ጥምረት አንድ የምርጫ ምልክት ቢጠቀሙም የፓርቲዎች ፖለቲካዊ ልዪነቶች እንዳሉ ናቸው ሲሉ አቶ ጽጋቡ ተናግረዋል።
የፓርቲዎች ጥምረት እስከ አንድ ፓርቲ መመስረት ድረስ ማደጉ ሀገራዊ ወጥ አጀንዳን ከመፍጠር አንጻር በጎ አስተዋጾ አለው ተብሏል።
ምላሽ ይስጡ