ነሐሴ 15 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በየጊዜው በወባ ዙሪያ በርካታ ጥናቶችን በማድረግ ላይ መሆኑን ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የወባና ትኩረት የሚሹ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገረመው ጣሰው ናቸው።
አሁን ላይ የወባ ስርጭት ማገርሸትን መነሻ በማድረግ ከሃገር ውጪ የሚገኝ የተሻለ የወባ መመርመሪያ ቴክኖሎጂ መገኘቱን ገልጸው ፤ መሳሪያው በትክክል እንደሚሰራና ከበፊቱ የተሻለ መሆኑን በጥናት በማረጋገጥ መሳሪያውን ወደ ሃገር ውስጥ በስፋት ተደራሽ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸው ፤ መሳሪያው በሰአት ከ55 እስከ 60 የሚደርሱ እዎችን ማስተናገድ የሚችል ከመሆኑም ባለፈ ካሁን ቀደም በሰዎች ስህተት የሚመጡ ወጤቶችንም የሚቀርፍ ነው ይላሉ።
መሳሪያው በተለይም የወባ ስጋት በስፋት ያለባቸው አከባቢዎች ላይ እንዲውል ለማድረግ ለባለሙያዎቹ በአጭር ስልጠና የማሳየት ስራ ብቻ የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸው ለነፍሰጡር ሴቶችና ለህጻናትም እንደሚያገለግልና የወባውን ደረጃ እና አይነት በሰፊው መለየት እንደሚያስችል አያይዘው አንስተዋል ።
በተጨማሪም አሁን ላይ ስርጭቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመሆኑ የወባ መድሃኒቶች በሽታውን ምን ያህል የመከላከል አቅም አላቸው በሚል ጥናት መደረጉን ገልጸው ፤ አሁን ለወባ ተብሎ እየተሰራጨ ያለው መድሃኒት በትክክል እንደሚሰራ በጥናት መረጋገጡንና ውጤቱ ለጤና ሚኒስቴር መላኩን ጠቅሰው ፤ የስርጭቱ መስፋፋት ምክንያት ለማወቅ ተጨማሪ ጥናቶች እየተደረጉ መሆናቸዉን አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ