ነሐሴ 15 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በዓለማችን እጅግ የላቁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምትታወቀው ጃፓን፣ የከተማዋን ውበት እና ቅልጥፍና ለማስጠበቅ የሚያስችል አውቶማቲክ የብስክሌት ማቆሚያ ስርዓት መዘርጋቷ ተገለጸ።
ይህ ስርዓት የብስክሌት ፓርኪንግን ዘመናዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል ተብሏል።
አሰራሩ እጅግ ቀላል ነው የተባለ ሲሆን ብስክሌት አሽከርካሪው ብስክሌቱን ከመሬት በላይ ባለው መግቢያ መድረክ ላይ ያስቀምጣል። ከዚያም የመታወቂያ ካርዱን ሲያሳልፍ፣ ሮቦቲክ ስርዓቱ ብስክሌቱን በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ በመሬት ስር በሚገኝ ክብ ቅርጽ ባለው እና ደህንነቱ በተጠበቀ ማከማቻ ውስጥ በአቀባዊ በማስገባት ያስቀምጣል ነው የተባለው።
ብስክሌቱን መልሶ ለማውጣትም በተመሳሳይ መልኩ ካርዱን መጠቀም ብቻ በቂ ሲሆን፣ ስርዓቱ ብስክሌቱን በፍጥነት ወደ ላይ መልሶ ያመጣዋል ነው የተባለው።
ይህ የላቀ ቴክኖሎጂ በተለይ በትልልቅ የትራንስፖርት መስመሮች ዙሪያ የሚታየውን የብስክሌት መጨናነቅ እና የመንገድ ዳር ውዥንብርን ያስቀራል ተብሏል።
በተጨማሪም፣ ብስክሌቶች ከዝናብ እና ከሌሎች የአየር ንብረት ሁኔታዎች የተጠበቁ እንዲሆኑ ያደርጋል የተባለ ሲሆን የቦታ አጠቃቀምን በእጅጉ ያሻሽላል ተብሏል።
ይህ ፈጠራ የጃፓንን ከፍተኛ ብቃትና የላቀ አደረጃጀት የሚያሳይ ምሳሌ ነው ተብሏል።
ምላሽ ይስጡ