ነሐሴ 15 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ጃፓን የሚገኙ ሳይንቲስቶች፣ የሰውን ልጅ ሚዛን ለመጠበቅ የሚረዳ፣ የእንስሳትን ጅራት የሚመስል ‘ሮቦቲክ ጅራት’ በመንደፍ ፈተና እያካሄዱ መሆኑ ተዘግቧል።
ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ በተለይ ለአረጋውያንና ለእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ሕይወት ለማሻሻል ያለመ ነው ተብሏል።
‘አርክ’ (Arque) የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ መሳሪያ፣ ወገብ ላይ የሚታሰር ሲሆን የሰውነትን እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ሴንሰር እና ሚዛን የሚያስጠብቁ ሞተሮችን ይጠቀማል ነው የተባለው።
ተጠቃሚው ሲራመድ፣ ሲታጠፍ ወይም ሲወጣና ሲወርድ ሚዛኑ እንዳይዛባ፣ ልክ እንደ እንስሳት ጅራት ተመጣጣኝ ክብደት በመጨመር ሰውነት ቀጥ ብሎ እንዲቆይ ያደርጋል ነው የተባለው።
ይህ ፈጠራ በዋነኝነት ለአረጋውያን የመውደቅ አደጋን ለመቀነስ እና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው የበለጠ መረጋጋት እንዲሰማቸው ለመርዳት ያለመ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም፣ በሕክምና ማገገሚያዎች፤ ከባድ ዕቃ በሚነሳበት የኢንዱስትሪ ሥራ እና በስፖርት ላይ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ሰፊ አቅም እንዳለው ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
የጃፓን ሳይንቲስቶች ይህንን ቴክኖሎጂ ወደ ተግባር ለማዋል ጠንካራ ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሰውን ሚዛን የማስጠበቅ ችሎታን በእጅጉ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።
ምላሽ ይስጡ