ነሐሴ 15 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የሩሲያ ነው የተባለ አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በምስራቅ ፖላንድ ውስጥ ተከስክሶ የእርሻ መሬትን በእሳት ማጋየቱን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ። ክስተቱን ተከትሎም በዋርሶ ከተማ የፀረ ሩሲያ ተቃውሞ መካሄዱ ተዘግቧል።
አደጋው የተከሰተው በምስራቅ ፖላንድ ገጠራማ አካባቢ ሲሆን፣ ድሮኑ ከተከሰከሰ በኋላ የበቆሎ ማሳ ውስጥ ከፍተኛ እሳት እንዲነሳ አድርጓል ነው የተባለው።
የአካባቢው የእሳት አደጋ ቡድኖች ወዲያውኑ ወደ ስፍራው በመድረስ እሳቱን ለመቆጣጠር ቢችሉም፣ ድሮኑ የመጣበትን ምክንያት እና ማን እንደላከው ለማጣራት ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ አደጋ ከተከሰተ በኋላ፣ በፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎዳና በመውጣት ሩሲያን የሚያወግዝ ተቃውሞ አድርገዋል። ተቃዋሚዎቹ “ሩሲያ ከፖላንድ ትውጣ” እና “የኔቶ መከላከያ ይጨምር” የሚሉ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን፣ የሩሲያ ድሮን በፖላንድ ግዛት ውስጥ መውደቁ የፖላንድን ሉዓላዊነት እንደመድፈር በመቁጠር ቁጣቸውን ገልጸዋል።
ፖላንድ የኔቶ አባል ሀገር እንደመሆኗ መጠን ይህ ክስተት የዲፕሎማሲ ውጥረትን ሊፈጥር እንደሚችል እየተነገረ ነው። ፖላንድ በጉዳዩ ላይ ከኔቶ አጋሮቿ ጋር እየተመካከረች መሆኑን አስታውቃለች።
ሩሲያ በበኩሏ ስለጉዳዩ እስካሁን ምንም አይነት አስተያየት አለመስጠቷም ተዘግቧል።
ምላሽ ይስጡ