ነሐሴ 13 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ዴንማርክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዜጎቿ ደስታ የምትታወቅ ሀገር ስትሆን፣ ይህ ስኬት ከልጅነት ጀምሮ በሚሰጡ ልዩ ትምህርቶች የተገነባ መሆኑ ተገልጿል። በተለይም ሀገሪቱ ከ6 እስከ 16 ዓመት ዕድሜ ክልል ለሚገኙ ህጻናት በየሳምንቱ የሚያገኙት “የርህራሄ ትምህርት” የዚህ ስኬት አንዱ ምሰሶ እንደሆነ ተዘግቧል።
ይህ ትምህርት ህጻናት የሌሎችን ስሜት እንዲረዱ፣ ርህራሄን እንዲያዳብሩ እና ከሌሎች ጋር በመተባበር እንዲሰሩ ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል። በትምህርቱ ወቅት ህጻናት ስለራሳቸው ስሜት እና ስለሌሎች ሰዎች ስሜት እንዴት ማውራት እንደሚችሉ ይማራሉ ነው የተባለው። የቡድን ፕሮጀክቶችን በመስራትም ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እና የተለያዩ አመለካከቶችን ለማዳመጥ ይለመዳሉ ተብሏል።
የዚህ ትምህርት ዋና ዓላማ ህጻናት ለወደፊቱ የተሻሉ ዜጎች፣ የቡድን አባላት እና መሪዎች እንዲሆኑ ማዘጋጀት ነው የተባለ ሲሆን ርህራሄ ከትምህርታዊ ውጤቶች በተጨማሪ የአእምሮ ጤናን እንደሚያሻሽል፣ የማህበራዊ ግንኙነቶችን እንደሚያጠናክር እና የመግባቢያ ክህሎቶችን እንደሚያጎለብት የብዙ ባለሙያዎች እምነት ነው፡፡
ዴንማርክ የርህራሄ ትምህርትን የትምህርት ሥርዓቷ አካል በማድረግ፣ ደስተኛና ምርታማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየጣለች መሆኗ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ሌሎች ሀገራት ሊወስዱት የሚገባ ምሳሌ ሊሆን ይችላልም ተብሏል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ