ነሐሴ 13 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ከቀናት በፊት የሲኖትራክ ተሽከርካሪ ያለበትን የጥራት እና የቴክኒክ ችግር ሳያሻሽል ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ መታገዱ የተገለጸ ሲሆን በጥራት ጉድለት፤ በየጊዜው ለሰው ልጆች ህይወት መጥፋት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት በመሆኑ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ስለ መከልከሉ የጉምሩክ ኮሚሽንን ጨምሮ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ስራ ተቋረጮች ማህበር ፕሬዝዳንት ኢንጅነር የሱፍ መሃመድ ተሽከርካሪው ባለፉት 20 ዓመታት በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በስፋት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት ከአስመጪዎች ጋር ውይይት መካሄድ ነበረበት ያሉት ፕሬዝደንቱ በድንገት የተወሰነ ውሳኔ ነው ሲሉም ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ የሚመለከታቸው አካላት በተቻለ መጠን ዘርፉ ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖን ሳያሳርፍ እና ጥራታቸውን ጠብቀው መግባት የሚችሉበትን አካሄድ መፍጠር እንደሚገባ ኢንጂነር የሱፍ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም ውሳኔው ከመወሰኑ አስቀድሞ ውይይቶችን ማድረግ ቢቻል በዘርፉ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በአንጻሩ መፍታት እና ማስተካከል የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር ይቻል ነበር ብለዋል፡፡ ማህበሩ ከሚመለከታቸው ባለ-ድርሻ አካላት ጋርም ውሳኔዎችን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝም ነው ፕሬዝዳንቱ ያስታወቁት፡፡
ሌላኛው ሀሳባቸውን የሰጡት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንቲኖስ በርኸተስፋ ተሽከርካሪው የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ ከመሆኑ ባለፈ ለግዢ የሚያስወጣው ወጪም ዝቅተኛ በመሆኑ በሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ሆኖም ውሳኔው መተላለፉን ተከትሎ ከሌሎች ሀገራት ጋር እንዲሁም ከአምራች ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ ውሳኔ ምክንያት የኮንስታራክሽን ዘርፉ ስራ እንዳይስተጓጎል ሌሎች ተኪ ተሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ