ነሐሴ 11 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በፍቅር መውደቅ እና አደንዛዥ እጽ መጠቀም በአንጎል ውስጥ ተመሳሳይ ምላሽ እንደሚፈጥር የሳይንስ ጥናቶች ማረጋገጣቸው ተዘገበ።
በፍቅር ስሜት ውስጥ መሆን አንጎልን ከሚቆጣጠረው ስርዓት (brain’s reward system) ጋር በተመሳሳይ መልኩ ምላሽ እንዲሰጥ ያደርገዋል የተባለ ሲሆን ይህ ደግሞ በኮኬይን ሱስ ወቅት ከሚከሰተው ሂደት ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ ግኝት በፍቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚሰማቸውን የደስታ ስሜትና መውሰናቸውን በሳይንሳዊ መንገድ ለመተርጎም ይረዳል ተብሏል።
አንድ ሰው በፍቅር ሲወድቅ አንጎል ከፍተኛ መጠን ያለው “ዶፓሚን” የተባለ ኬሚካል ያመነጫል ነው የተባለው።
ዶፓሚን ከደስታና ከመነሳሳት ስሜት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው ተብሏል።
የስነ-አዕምሮ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ ይህ የዶፓሚን ፍሰት በኮኬይን ወይም በሌሎች ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮች በሚወሰዱበት ጊዜ ከሚፈጠረው የኬሚካል ምላሽ ጋር ተመሳሳይ ነው ብለዋል።
በመሆኑም፣ አዲሱ ፍቅር የሚፈጥረው የደስታ ስሜት እና የፍቅረኛውን መልክ የማየት ፍላጎት በሳይንሳዊ መንገድ ሲታይ እንደ ሱስ ባህሪ ሊገለጽ ይችላል ተብሏል።
ይህ ጥናት ፍቅርን እንደ ስሜታዊ ገጠመኝ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ባዮሎጂያዊ እና ኬሚካላዊ ሂደት እንድንመለከተው ያደርጋል ነው የተባለው።
የፍቅር ስሜት የሚያስከትለው አዎንታዊ ስሜት፣ ለሰዎች ስነ-ልቦናዊና አካላዊ ጤንነት ጠቃሚ ቢሆንም፣ ይህ ኃይለኛ የዶፓሚን ፍሰት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ