ነሐሴ 11 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በጃፓን የሚገኘው “ሺንካንሰን” የተሰኘው ፈጣን ባቡር አገልግሎት ከ60 ዓመታት በላይ ባስቆጠረው ታሪኩ አንድም ገዳይ አደጋ ወይም ባቡር ከሀዲድ ወጥቶ መገልበጥ አጋጥሞት እንደማያውቅ ተገለጸ።
ይህ ባቡር በዓለም ላይ ካሉ የፈጣን ባቡር መስመሮች ሁሉ እጅግ አስተማማኝ መሆኑን የሚያሳይ ነው ተብሎለታል።
ባቡሩ ከ1964 ዓ.ም ጀምሮ ከ10 ቢሊዮን በላይ መንገደኞችን ያለምንም ገዳይ አደጋ አጓጉዟል የተባለ ሲሆን ምንም እንኳን እ.ኤ.አ. በ2004 በቹኤትሱ የመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት ባቡሩ ከሀዲድ ወጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ባቡሩ ላይ የነበሩ 155 ተሳፋሪዎች ምንም አይነት ከባድ ጉዳት አልደረሰባቸውም ተብሏል።
የሺንካንሰን ስኬት ቁልፍ ምስጢሮች መካከል አንዱ እጅግ በጣም ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መሆኑ የተመላከተ ሲሆን ባቡሩ በሰዓት እስከ 320 ኪሎሜትር ፍጥነት የሚጓዝ ሲሆን፣ አማካይ መዘግየቱ 1.6 ደቂቃ ብቻ ነው ተብሏል።
ይህ አስገራሚ ትክክለኛነት በጃፓን ባቡር መስመር ላይ ባሉ ባለሙያዎች ጥልቅ የጥገና እና የስራ ቅንጅት የተገኘ ውጤት ነው ተብሏል። በተጨማሪም፣ ለመሬት መንቀጥቀጥ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ ዘመናዊ ስርዓቶች ባቡሩን ከመሬት መንቀጥቀጥ በፊት በራስ-ሰር እንዲቆም በማድረግ ለደህንነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሏል።
በዚህም ምክንያት፣ የጃፓኑ ሺንካንሰን በዓለም ላይ ለሌሎች ሀገራት የፈጣን ባቡር መመዘኛ እና ምሳሌ ሆኖ ቀጥሏል ነው የተባለው።
በጌታሁን አስናቀ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ