ነሐሴ 12 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢፌዴሪ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የመንግስት ሰራተኞችን የደሞዝ ማሻሻያ ተከትሎ፣ አንዳንድ ነጋዴዎች ባልተገባ መልኩ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው፣ የደሞዝ ጭማሪው የሰራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያለመ በጎ ተግባር መሆኑን አውቆ፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ አሳስቧል።
መግለጫው የደሞዝ ማሻሻያው የአገሪቱን ከ2% የማይበልጥ የመንግስት ሰራተኛን ኑሮ በማሻሻል የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሳደግ ታስቦ የተደረገ መሆኑን አብራርቷል።
በአዋጅ ቁጥር 980/2008 እና 813/2006 እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ህግ መሰረት፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ምርት በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት የሚፈጥሩ ወይም አላግባብ ምርት የሚያከማቹ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።
በተጨማሪም የሚኒስቴሩ የንግድ መዋቅሮች ከፍትህና ፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የገበያ ማረጋጋትና ቁጥጥር ስራዎችን በማጠናከር በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልጿል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ