ነሐሴ 12 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ)የዝናብ ወቅት ለዶሮ በሽታ አምጪ ተህዋስያን መራባትና መስፋፋት አመቺ በመሆኑ፣ መንግስት የባለሙያ ድጋፍና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጠ ቢሆንም፣ በዘንድሮው ክረምት በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱት ወረርሽኞች ግን በአብዛኛው በአርቢዎች የዕውቀትና የአያያዝ ጉድለት ምክንያት መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ለመናኸሪያ ሬዲዮ ገልጿል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤናና ቬተርነሪ ፐብሊክ ሄልዝ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ሜሮን ሞገስ እንደገለጹት፣ የዝናብ ወቅት የዶሮ በሽታ አምጪ ተህዋስያን እንዲራቡና በቀላሉ እንዲተላለፉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ከፍተኛ እርጥበትና የውሃ አቅርቦት መበከል ለዚህ ዋና ምክንያት ሲሆን፣ በሀገራችን በዝናብ ወቅት ከሚጠበቁ የዶሮ በሽታዎች መካከል የኒውካስትል ወይም የዶሮ ፈንግል በሽታ ይጠቀሳል ብለዋል።
ይህንን ለመከላከል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ባለሙያዎችን በመላክ ለዶሮ አርቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጠ መሆኑንም ኃላፊዋ ገልጸዋል። በዘንድሮው ክረምት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የዶሮ በሽታ እንደ ወረርሽኝ መከሰቱን እንስተው፤ ሆኖም ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የተፈጥሮ ሁኔታና የሚጠበቀው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ሳይሆን የአርቢዎች የአያያዝ ጉድለት መሆኑን ዶክተር ሜሮን ተናግረዋል።
በሽታ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የቅድመ ጥንቃቄና የሞቱ ዶሮዎችን አወጋገድ በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራቱን ጠቁመው፣ በሌሎች አካባቢዎችም እንዳይከሰት ይህንንን ተግባር አጠናክረው መቀጠላቸውን አስረድተዋል።
በተለይ በዝናባማ ወቅት የሚከሰተውን የእርጥበትና የውሃ መበከል ስጋት ለመቀነስ ጥንቃቄ ማድረግ፣ እንዲሁም የበሽታ ምልክት ሲታይ አርቢዎች የባለሙያ ድጋፍ መጠየቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ