ነሐሴ 12 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ) የቼክ ሪፐብሊክ መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ተንቀሳቃሽነት እና ነጻነት ለማሻሻል ያለመ አዲስ አሰራር በይፋ ተግባራዊ አድርጓል።
አዲሱ የህዝብ ካርታ ፕሮግራም፣ በተለይም የተሽከርካሪ ወንበር ተጠቃሚዎችን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ በአውሮፓ ውስጥ እንደ አርአያነት ሊጠቀስ የሚችል እርምጃ ተብሎ ተሞካሽቷል።
ይህ አዲስ የዲጂታል ካርታ የአካል ጉዳተኞች በቀላሉ እና በአስተማማኝ ሁኔታ መንቀሳቀስ የሚችሉባቸውን ደረጃ የሌላቸው (step-free) እና ምቹ የሆኑ መንገዶችን በግልጽ የሚያመለክት ነው ተብሏል።
ፕሮግራሙ የተሽከርካሪ ወንበር ተጠቃሚዎች የጉዞ መስመራቸውን አስቀድመው እንዲያቅዱ እና በመንገዳቸው ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰናክሎችን እንዲያስወግዱ ያስችላቸዋል ነው የተባለው።
የቼክ ሪፐብሊክ ባለስልጣናት ይህ ዕቅድ የአካል ጉዳተኞችን በራስ የመተማመን ስሜት ከማሳደግ ባሻገር፣ በሕዝብ ቦታዎች ያላቸውን ተሳትፎ እንደሚያጎለብት ገልጸዋል።
ይህ አዲስ አሰራር አካታች ማህበረሰብ ለመፍጠር እና የሁሉም ዜጎች ተንቀሳቃሽነት መብትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት አካል ነው ተብሎ ተወስዷል።
በበርካታ ከተሞች የህዝብ ትራንስፖርት ጣቢያዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችን እና የመዝናኛ ስፍራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ያሉ ተደራሽ መንገዶችን የያዘው ይህ ካርታ፣ የአካል ጉዳተኞችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ቀላል እና አስተማማኝ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ፕሮግራም የቼክ ሪፐብሊክ በአካል ጉዳተኞች መብት ዙሪያ እያደረገች ያለውን ጥረት የሚያሳይ ሲሆን፣ ለሌሎች ሀገራትም አርአያ ሊሆን እንደሚችል ተዘግቧል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ