👉የንፅህና አባዜ ወይስ የህልውና ጥበብ?
ነሐሴ 11 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በረሮዎች ብዙውን ጊዜ ከቆሻሻ ጋር በተያያዘ ስማቸው የሚነሳ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባህሪያቸው ላይ የሚደረጉ ምልከታዎች ግን እጅግ በጣም ንቁ የሆኑ የንፅህና ጠባቂዎች መሆናቸውን ያመለክታሉ።
በተለይም ሰውን ከነኩ በኋላ ወዲያውኑ እራሳቸውን የማፅዳት ልማድ ያላቸው ሲሆን፣ ይህ ድርጊት ከሰው ልጅ የ”መጸየፍ” ስሜት ይልቅ ለህልውናቸው አስፈላጊ ከሆኑ ምክንያቶች የመነጨ መሆኑ ታውቋል።
የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚያብራሩት፣ በረሮዎች አንቴናዎቻቸውና እግሮቻቸው ላይ ከፍተኛ የስሜት ህዋሳት አሏቸው። እነዚህ የስሜት ህዋሳት ምግብን ለማግኘት፣ አደጋን ለማስወገድ እና አካባቢያቸውን ለመረዳት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
ከሰው ቆዳ የሚተላለፉ ዘይቶች፣ ላብ እና ያልተለመዱ ኬሚካሎች የእነዚህን የስሜት ህዋሳት ትክክለኛነት ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ ነው የተባለው።
ስለሆነም፣ በረሮዎች ከሰው ንክኪ በኋላ ራሳቸውን ሲያፀዱ፣ የህይወት መትረፊያ መንገዳቸውን እየተገበሩ ነው መሆኑ ተመላክቷል።
ይህ የንፅህና አጠባበቅ ተግባር የስሜት ህዋሳቶቻቸውን ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው በመመለስ፣ በአካባቢያቸው ውስጥ ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል ተብሏል። በመሆኑም፣ የ”ንፅህና አባዜ” የሚመስለው ባህሪያቸው በዋናነት ለህልውናቸው ወሳኝ የሆነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንጂ ስሜታዊ ምላሽ አይደለም ተብሏል።
ይህ ግኝት በረሮዎችን በተመለከተ ያለንን ግንዛቤ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ እነዚህ ፍጥረታት ያላቸውን ውስብስብ የህልውና ስልቶች ዳግም እንድናጤን ያደርገናል ተብሏል።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ