ነሐሴ 12 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ)በክልሉ አሁን ላይ ለውሃ ማጣሪያነት የሚያገለግል ምንም አይነት ኬሚካል አለመኖሩንና በከፍተኛ ሁኔታ የኮሌራ ስርጭት መበራከቱን ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት በትግራይ ክልል ዉሃና ኢነርጂ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሃይለኪሮስ ከለል ናቸው።
የውሃ ማውጫ ጉድጓዶችን ለማከም የሚረዱ ኬሚካሎች ባለመኖራቸው የአከባቢው ማህበረሰብ ወሃ አፍልቶ እንዲጠቀም ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው ፤ በክልሉ እርዳታ የሚያደርጉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አልፎ አልፎ እያደረጉ ባለው እንደውሃ አጋር ያሉ የማከሚያ መድሃኒቶች ድጋፍና ከሰሞኑ በእርዳታነት የመጡ ወደ 200 የሚጠጉ የውሃ ማጣሪያ ባልዲዎችን የማሰራጨት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል ።
በተለይም በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታ ላይ የሚገኙ ሁለት ወረዳዎች 113 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ መያዛቸውንና 3 ሰው መሞቱን ጠቅሰው ፤ የውሃና ኢነርጂ ቢሮው ከክልሉ የጤና ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ከውሃ ማከሚያ መድሃኒት አጠቃቀምና ስርጭት ጋር በተያያዘ በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።
የፌደራል መንግስትም ሆነ የክልሉ የጊዜያዊ አስተዳደር የተደረገውን የእርዳታ ጥሪ ተቀብሎ ምንም አይነት ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ የግብ-ረሰናይ ድርጅቶቹ ግን ሁለተኛ ዙር ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸዉንና ይሄን እየተጠባበቁ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኮሌራ ስርጭቱ እንደሚጨምር አመላካች ነገሮች አሉ ያሉት አቶ ሃይለኪሮስ ፤ አሁን ላይ በቢሮው በኩል የንጹህ ወሃ አቅርቦቱን ለማሻሻል የሚረዱ ምንም አይነት የመድሃኒት ግብዓት አለመኖሩና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ደጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ምላሽ ይስጡ