ነሐሴ 08 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ) እንደ ሀገር በገዳይነቱ እየታወቀ የመጣው የኩላሊት በሽታ ትኩረት ተሰጥቶት በቂ ጥናት እየተደረገበት አለመሆኑን የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት አስታውቋል።
የኩላሊት በሽታ እንደ አለም በ16ኛ ደረጃ ገዳይ ሆኖ መመዝገቡንና ይህንንም የአለም ጤና ድርጅት እንዳጠናው የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሰለሞን አሰፋ ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ በ2040 5ኛ ደረጃን ይይዛል ተብሎ ይጠበቃልም ሲሉ ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል። የአለም የጤና ድርጅት በዚህ ልክ በየጊዜው አንገብጋቢነቱን እያጠና ቢያወጣም በኢትዮጵያ በኩል ግን አናሳ የዳሰሳ ጥናቶች ብቻ እንደሚካሄዱና በቂ ጥናት የማድረግ ልማድ እንደሌለ ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል። በመሆኑም የጤና ዘርፉን በሚመሩት አካላትና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶት ጥናት እንዲደረግበት ግፊት እያደረጉ እንደሚገኙም ዶ/ር ሰለሞን ገልጸዋል።
ልመናን የማበረታታት አላማ የለንም ያሉት ዋና አስራ አስኪያጁ ነገር ግን በመኪና እየዞሩ በመንገድ ዳር ሲለምኑ የሚገኙ የኩላሊት ህመምተኞችም መከልከላቸው ትክክለኞቹን ታማሚዎች የጎዳ ተግባር ነው ብለዋል። አጭበርባሪዎችም አሉ በሚል ምክንያት እውነተኞቹንም አብሮ የጎዳ ተግባር ነው ያሉት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ብዙዎቹ በዚያ መንገድ በሚያገኙት የህብረተሰብ ድጋፍ መታከም ችለው እንደነበርም ገልጸዋል።
አምራች ዜጎችን እየቀጠፈ የሚገኘው የኩላሊት ህመም በጥናት ተለይቶና ተስፋፍቶ መፍትሄ የሚሻው ጉዳይ ነው ሲል በጎ አድራጎት ድርጅቱ በአጽንኦት ተናግሯል።
ምላሽ ይስጡ