ነሐሴ 08 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ) በአንድ ወቅት የሞባይል ስልክ ኢንዱስትሪን በመምራት ይታወቅ የነበረው ኖኪያ፣ በቴክኖሎጂው ዓለም በፍጥነት መለዋወጥ ምክንያት ከገበያ ውጭ በሆነበት ወቅት፣ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት ስቴፈን ኢሎፕ ማይክሮሶፍት ኖኪያን መግዛቱን ባስታወቁበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንባቸውን አፍስሰዋል።
በዚህ ስሜታዊ ንግግራቸው፣ ኢሎፕ “ምንም ስህተት አልሰራንም፣ ነገር ግን በሆነ መንገድ ተሸነፍን” ሲሉ ተናግረዋል። ይህ አባባል ኖኪያ በንግድ ሥራው ትልቅ ስህተት ባይሠራም፣ የሞባይል ኢንዱስትሪው በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ ከአፕል እና አንድሮይድ አምራቾች ጋር መወዳደር እንዳልቻለ ያመለክታል።
የኩባንያው ውድቀት የስትራቴጂክ ስህተቶች እና ወደ ስማርት ስልኮች ለመሸጋገር የተፈጠረ መዘግየት ውጤት እንደሆነ ቢታመንም፣ የኢሎፕ ንግግር በዘመናዊው ገበያ ላይ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣልነው የተባለው። ኩባንያዎች የገበያ ለውጦችን ለመቀበል እና ለመላመድ ካልቻሉ፣ ትርፋማነትን ማጣት ብቻ ሳይሆን ከውድድር ሙሉ በሙሉ የመውጣት አደጋ እንደሚገጥማቸው ተመላክቷል።
ምንም እንኳን የኖኪያ የንግድ ሞዴል እና ምርቶች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ቢሆኑም፣ በፍጥነት የሚለዋወጠውን የደንበኞችን ፍላጎት መረዳት እና ለውጡን አለመቀበል፣ ለታላቁ ኩባንያ ውድቀት ምክንያት ሆኗል ነው የተባለው።
የኢሎፕ ንግግር የአንድ ታላቅ ኩባንያ ውድቀት ያስከተለውን ስሜታዊ ጫና የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህ ታሪክ ብዙ የንግድ ሥራ መሪዎች ስለ ለውጥ አስፈላጊነት እንዲያስቡበት አድርጓል ተብሏል።
ምላሽ ይስጡ